Monday, May 28, 2018

የሰማዕታትን አደራ እንጠብቅ

(May 28, (ርዕሰ አንቀፅ))--ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር ናት፡፡ ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ የአኗኗር ዘይቤዎች አላት፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሥርዓቶች እነዚህን ልዩነቶች አምኖ የሚቀበል መንግሥት አልነበረም። ይልቁንም ልዩነቶችን ለመደፍጠጥ በሚደረገው ግብግብ የብሔር ጭቆና፣ የአርሶና አርብቶ አደሩ ከመሬት መፈናቀል፣ የመልማት መብት መነፈግ እንዲሁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት በመስፈኑ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ለትጥቅ ትግል እንዲነሱ አደረገ።

ይህንን የሕዝብ ጭቆና ሥርዓት ለመገርሰስ ለትጥቅ ትግል በረሃ የገቡ በርካታ የኢትዮጵያ ልጆችም በእነዚያ መራር የትግል ዓመታት ተሰውተዋል፤ በርካቶችም አካላቸውን አጥተዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ዓላማቸው ከራሳቸውም በላይ ወገኖቻቸውን ነፃ ማውጣት በመሆኑ ከ17 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በግንቦት 20 ድል የትጥቅ ትግሉ መቋጫ አግኝቷል፡፡ የሀገራችን ሕዝቦችም የትግላቸውን ፍሬ ማየት ችለዋል፡፡ አምባገነናዊውን ሥርዓት ከጣሉ በኋላ ወደው እና ፈቅደው ባጸደቁት ሕገመንግሥት ላይ ተመስርተው በገነቡት ፌዴራላዊ ሥርዓትም ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ተጎናፅፈዋል፡፡

ሰማዕታቱ በደማቸው ካጎናፀፉን መብቶች ውስጥ ዋነኛው ሕገመንግሥታችን ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት የአገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ማስከበር የቻለ ነው፡፡

ሕገመንግሥቱ ከያዛቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሕዝብን ሉኣላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጠው አንቀፅ ስምንት ይጠቀሳል፡፡ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ አንድ ላይ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸው ተደንግጓል፡፡ ሉአላዊነታቸውም በሕገመንግሥቱ መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲዊ ተሳትፎ አማካይነት እንደሆነ ሰፍሯል፡፡

በዚህ ሕገመንግሥት የተገለፀውን የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብት ለማስከበር የኢፌዴሪ መንግሥት የተከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓትን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሀገራችን ሕዝቦች ቀድሞውንም ሲታገሉለት ከነበረው የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ጋር በቀጥታ የተቆራኘ በመሆኑ ይህን ሥርዓት በኋላ ለመጡ ስኬቶችም መሠረት መሆን ችሏል፡፡

በዚህ የተነሳም የፌዴራል ሥርዓቱ በርካታ ትሩፋቶችን አስገኝቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ በኢኮኖሚው ላይ የተገኘው ስኬት ይጠቀሳል፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ ላለፉት 15 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ 10 ነጥብ 1 ከመቶ በማደግ በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ አገራት ግንባር ቀደም እንድንሆን አስችሎናል፡፡ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢንም በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ በአማካይ 800 ዶላር ማድረስ የተቻለ ሲሆን የአገራችን መገለጫ ሆኖ የቆየውን ድህነትም በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ከ44 በመቶ በላይ የነበረው ድህነት መጠን ወደ 22 ከመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡

በ1987 ዓ.ም 48 ዓመት የነበረውን የአገራችንን ዜጎች አማካይ የመኖር ዕድሜም አሁን ወደ 65 ዓመት ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመሠረተ ልማት፣ በማህበራዊ ዘርፍ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፎችም ባለፉት 27 ዓመታት የተመገዘገቡት ለውጦች ከእኛ አልፈው የዓለምን ማህበረሰብና መንግሥታት ጭምር ያስገረሙ ናቸው፡፡ ይህ ውጤት በሰማእታቱ የተገኘ ነው፡፡

መስዋእትነት የከፈሉትን ለዚሁ ነው፡፡ ስለሆነም ውጤቱን በማስቀጠል አደራቸውን መጠበቅ አለብን፡፡ በሌላ በኩል አገራችን ለዘመናት ተጭኗት ከቆየው የከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ተላቃ በአጭር ጊዜ መካከለኛ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችው እቅድ እውን እንዲሆን የአገራችን ኢኮኖሚ አሁን እየተጓዘበት ካለው ፍጥነት በላይ መፍጠን፣ ሕዝባችንም አሁን እየሰራ ከሚገኝበት የሥራ ባህል ወጥቶ የፀረ ድህነት ትግሉን ማቀጣጠል አለበት፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ፈተናዎችና ችግሮችን ከስር ከስሩ እየፈታ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡

ከነዚህ ፈተናዎችም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የዴሞክራሲዊ ብሔርተኝነት አለመዳበር፣ ልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነቱን አለመያዝ፣ በየደረጃው የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመፈታት ይልቅ እየሰፉ መምጣት፣ የከረረ ብሔርተኝነት፣ የሃይማኖት ጽንፈኝነት፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በአግባቡ አለመተግበር እና መሰል ችግሮች ዋና ዋዎቹ ናቸው፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ራሱን በራሱ እያረመ ተጨማሪ ድል እያስመዘገበ የሚሄድ ጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት መገንባት፣ የሕዝቡን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ሌብነትን የሚፀየፍ ማህበረሰብ መገንባት እንዲሁም ኅብረብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ለአገራዊ እድገት መትጋት ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም የዜጎች እኩል ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ በታሪክ አጋጣሚ ወደኋላ ለቀሩ ክልሎችና አካባቢዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እርስ በእርስ ተደጋግፈው የሚሄዱበትና የአገራችን ልማትም ተመጣጣኝና ፍትሃዊ እንዲሆን መስራት ይጠበቃል፡፡ ችግሮችን መፍታት የሰማዕታትን አደራ መጠበቅ ነው፡፡ በችግሮች ተጠልፎ ሥርዓቱን አደጋ ላይ መጣል ተገቢ አይደለም፡፡ አደራን መወጣት አለመቻልም ነው፡፡

ስለሆነም ሰማዕታት ትተውልን ያለፉት አደራ እውን እንዲሆን የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ ማፋጠንና የሥርዓቱ አደጋ የሆኑ ችግሮች በአፋጣኝ መፍታት ይገባል፡፡ መላው የሀገራችን ሕዝቦች በተለይ ደግሞ በየደረጃው ያለው አመራር ኃላፊነቱን በሚገባ በመወጣት የሰማዕታቱን አደራ እንጠብቅ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ርዕሰ አንቀፅ)

No comments:

Post a Comment