Saturday, May 26, 2018

ኤርትራ የቀረበላትን የሰላም ጥሪ ልትቀበለው ይገባል!

((May 26, 2018, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ግጭት የተጀመረበት ሃያኛ ዓመት ላይ እንገኛለን፡፡ የኤርትራ መንግሥት በታንክ የታገዘ ሠራዊት በአካባቢው የነበሩ ሚሊሻዎችና ፖሊሶችን በማጥቃት ባድመን የተቆጣጠረው ግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ወረራ ከተፈጸመበት ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ቅድሚያ ለሰላም በመስጠት ችግሩን በውይይት ለመፍታት የሰላም እጃቸውን ዘርግተው ነበር፤ ተቀባይ አላገኘም እንጂ፡፡

መጀመሪያ በሩዋንዳ መንግሥት፤ ቀጥሎም በአሜሪካ መንግሥት እንዲሁም ሌሎች ወገኖች ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኤርትራ መንግሥት በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ለቅቆ እንዲወጣ ቢጠየቅም ጆሮ ዳባ ልበስ በማለቱ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሰላም ጥሪዎች ከሽፈዋል፡፡ በመሆኑም ሁለት ዓመት የፈጀ ጦርነት ተካሂዶ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራለች፡፡

ከጦርነቱ ማብቃት ማግስትም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ነገሮች ወደነበሩበት ይመለሱ ዘንድ የሰላም እጃቸውን ከመዘርጋት አልተቆጠቡም፡፡ዛሬም ድረስ ለሰላም ያላቸው አቋም አልተለወጠም፡፡

የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች በባህል፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና ሥነ ልቦና አንድ በመሆናቸው በጋራ ማደግና ከድህነት መውጣት የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መኖሩን የተገነዘቡት የሀገራችን መንግሥትና ሕዝብ እጃቸውን ለሰላም ከዘረጉበት ወቅት አንስቶ እስከአሁን ድረስ ስለሰላምና በጋራ አብሮ ስለማደግ ሲሉ የዘረጉት እጅ አልታጠፈም፡፡ በኤርትራ በኩል ግን አሁንም ግትር አቋም በያዘ ሥርዓት ምክንያት እንኳን በራሱ ተነሳሽነት ሰላም ሊፈጥር ቀርቶ የቀረበለትን ሰላም መቀበል አልቻለም፡፡ ይህ አቋሙ በዋናነት የኤርትራ

ሕዝብን ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም ለኢትዮጵያና ለአካባቢው ሀገሮች ከመልካም ጉርብትና ይገኝ የነበረውን ጥቅምም አሳጥቷል፡፡ ስለሆነም ዛሬም የሰላም ጥሪ ይቀበል ዘንድ እናሳስባለን፡፡

ከታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ጀምሮ እስከ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ድረስ ለኤርትራ መንግሥት የሰላም ጥሪ ቀርቧል፡፡የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለሰላም ሲባል አስመራ ድረስ ሄደው ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ ይህም የሚያሳው የኢትዮጵያ መሪዎች ለሰላም ያላቸውን የማይናወጥ አቋም ነው፡፡በኤርትራ በኩል ያለው አመራርና ሥርዓት ግን አሁንም በግትር አቋሙ በመጽናቱ ሁለቱ ሕዝቦችና ሀገራት ከሰላም ሊያገኙት የሚገባ ጥቅም ማግኘት ሳይችሉ ሃያ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ነባራዊ ሁኔታ መለወጥ አለበት፡፡

ለሰላምና ለመልካም ጉርብትና ዋጋ የሚሰጥ አስተሳሰብ በኤርትራውያን በኩል መምጣት ይኖርበታል፡፡ ችግሮችንና ልዩነቶችን በውይይትና በሰጥቶ መቀብል መርህ መፍታት እየተቻለ የሁለቱን ሀገሮች ሕዝቦች ከሰላምና ከመልካም ጉርብትና ተጠቃሚነት ማራቅ ተገቢ አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር «ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን።

የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለፅኩ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ» ሲሉ መግለጻቸው አሁንም በኢትዮጵያ በኩል ለሰላም የተዘረጋው እጅ አለመታጠፉን ማረጋገጫ ነው፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ኤርትራ ልትቀበለው ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ርዕሰ አንቀፅ)

No comments:

Post a Comment