Monday, May 28, 2018

የግንቦት 20 ትሩፋቶች

(May 28, (አጀንዳ))--ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት ከተጫናቸው የሰላም እጦት ችግር ተላቀው ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ በር የከፈተ ዕለት ነው፡፡ የዘመናት የሕዝብ ብሶት የወለደውና መላውን ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈው በኢህአዴግ የተመራው የትጥቅ ትግል በ1983 ዓ.ም ዜጎችን ከታሰሩበት የጭቆና ቀንበር በማላቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር በር የከፈተ ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን ደርግ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር በሚል መርህ የአገሪቱን ሀብትና ንብረት ሁሉ ለጦርነት በማዋሉ ኢህአዴግ ወደ መንበረ ሥልጣን ሲመጣ አገሪቱ ካፒታል አልባና የመንግሥት ካዝናም ባዶ ነበር፡፡ ሥርዓቱም ዜጎች በአገራቸው ላይ ሰርተው ሀብት እንዳያፈሩና ለሌሎችም የሥራ ዕድል እንዳይከፍቱ ያደረገ ስለነበር በአገሪቱ የሥራ ዕድል በመንግሥት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡

በእነዚህና ሌሎች ችግሮች የተነሳም ኢህአዴግ ሥልጣን ሲረከብ በርካታ ፈተናዎች ከፊቱ ተጋርጠው ነበር፡፡ በአንድ በኩል ለዘመናት በጦርነት ውስጥ የቆየው አገሪቱ ኢኮኖሚ ባዶ ካዝና መሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱን ዜጎች ጠፍንጎ የያዘው ድህነትና ኋቀርነት በቀላሉ የሚናድ አልነበረም፡፡

ኢህአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስትም ዋነኛው ጉዳይ ይኸው ድህነትና ኋላቀርነት መሆኑን በመገንዘብ በፀረ ድህነት ዘመቻ ላይ ለመረባረብ ወሰነ፡፡ በ1987ዓ.ም ለሕዝቦች የሰላምና የአንድነት ዋስትና የሰጣቸውን ሕገመንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ካፀደቀ በኋላም ትኩረቱን ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት አደረገ፡፡

ሆኖም የተጀመረው ልማት በአጭር ጊዜ የታሰበውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ በተለይ ተራቁቶ የቆየውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ ትግልን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ፈተናው ቀላል አልነበረም፡፡ ከልማታዊ አስተሳሰብና እድገት ይልቅ በጦርነትና በግጭት መንፈስ ውስጥ የኖረው ሕዝብም ቢሆን ይህንን የለውጥ እንቅስቃሴ ቶሎ ተቀብሎ ወደ ትግበራ ሊገባ አልቻለም፡፡

መንግሥትም ሙሉ ለሙሉ በልማት ሥራው ላይ በማተኮር ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን ማድረጉን ተያያዘው፡፡ ሆኖም የአገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት ሲጀምር ሌላ ፈተና ከፊት ለፊት ተጋረጠ፤ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን አገሪቱን ለድህነትና ለኋላቀርነት የዳረገው ጦርነት በመሆኑ ኢትዮጵያ ወደዚህ ጦርነት ለመግባት ፍላጎት ባይኖራትም ግጭትን መከላከል የሚቻለው በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ባለመሆኑ ጦርነቱ አይቀሬ ሆነ፡፡

በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ አሸናፊ ብትሆንም መነቃቃትን ማሳየት ላይ ለነበረው የአገራችን ኢኮኖሚ ግን ታጥቦ ጭቃ ሆኖበት የተነቃቃው ኢኮኖሚ መልሶ ወደኋላ ተመለሰ፡፡ በዚህም የተነሳ የፀረ-ድህነት ትግሉ እንደገና ከባድ ፈተና ገጠመው፡፡ ሆኖም መንግሥት ቀድሞውንም ቢሆን ለሕዝቦች ሉዓላዊነትና ነፃነት እንዲሁም ለአገሪቱ ብልፅግና እውን መሆን የቆመ በመሆኑ እነዚህ እንቅፋቶች ሊያቆሙት አልቻሉም፡፡ ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን መልሶ ሕዝቡን በማስተባበር ፊቱን ወደ ልማት መለሰ፡፡

ከጦርነቱ በኋላ በነበረው የፀረ ድህነት ትግል ግን አዲስ ስልት መቀየስ የግድ ነበር፡፡ በነበረው የቁጥ ቁጥ የልማት አካሄድ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አዳጋች መሆኑን የተረዳው መንግሥት ከዚህ ለመውጣት ስር ነቀል የኢኮኖሚ ሽግግር ማካሄድ ተገቢ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እውን አደረገ፡፡የመጀመሪያው እቅድ (ሁለተኛው እቅድ በሂደት ላይ ያለ መሆኑ ታሳቢ በማድረግ) አፈጻጻም መሠረት አድርገን የግንቦት ሃያ ትሩፋቶችን ማየት እንችላለን ፡፡

የመጀመሪያው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድም አራት መሠረታዊ ዓላማዎችን መሠረት በማድረግ የታቀደ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነዚህም ኢኮኖሚውን በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ 11 በመቶ በማሳደግ የሚሌኒየም የልማት ግቦችን ማሳካት፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎት ሽፋንን በመጨመርና ጥራቱን በማረጋገጥ ላይ የተመሠረተ ማህበራዊ ልማት በማካሄድ የሚሌኒየም ልማት ማህበራዊ ግቦችን ማሳካት፣ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግሥትን በመፍጠርና በማጠናከር ለቀጣይ የሀገር ግንባታ ሥራ ምቹ መደላድል መፍጠር እና የተረጋጋ ማክሮ- ኢኮኖሚ በማስፈን የልማቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ናቸው፡፡

ዕቅዱ ከ2003 ዓ.ም በፊት በነበሩት ሰባት ዓመታት የተመዘገበውን ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት የማረጋገጥ ግብ ያስቀመጠ እንደነበር የእቅድ አፈጻፀም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በዚህም መሠረት በየዓመቱ በአማካይ በ10.1 በመቶ ማደግ ችሏል፡፡ የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ከሰሃራ-በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀርም በእጥፍ የበለጠ እንደሆነ ማየት ተችሏል፡፡

የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ሰፊ እውቅናና ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡ ዓመታዊ አማካይ የነፍስ-ወከፍ ገቢም በ2002 ከነበረበት 377 የአሜሪካን ዶላር በ2007 መጨረሻ ወደ 691 የአሜሪካን ዶላር እንዲያድግ አስችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ 800 አሜሪካን ዶላር መድረስ ችሏል፡፡ ይህ ፈጣን የነፍስ ወከፍ ገቢ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ማህበራዊ ልማት እና የአደጋ ተጋላጭነትን በመቋቋም አቅም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተደረገ በ2017 ዓ.ም ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተቀመጠውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል እንደሆነም የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል የአገራችን የድህነት ምጣኔ በ1997ዓ.ም የበጀት ዓመት 38.7 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በ2003 የበጀት ዓመት በተካሄደ ተመሳሳይ ጥናት ይህ ምጣኔ ወደ 29.6 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በያዝነው ዓመት ደግሞ ምጣኔው እስከ 22 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ድህነትን በግማሽ መቀነስ የሚለው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ማሳካት ያስቻለን አፈፃፀም እንደሆነ ይታመናል፡፡ የድህነት ምጣኔው በፍጥነት እየቀነሰ የመጣው በዋናነት በተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ሳቢያ እንደሆነ የተደረጉት ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ በአማካይ በ6.6 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ በአማካይ በየዓመቱ በ10.8 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ በአማካይ በየዓመቱ በ20.2 በመቶ አድጓል፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አካል የሆነው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በተጠቀሱት አምስት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ በ14.6 በመቶ ማደግ ችሏል፡፡

በዕቅድ ዘመኑ ዋናው የዕድገት ምንጭ የግብርና ዘርፍ እንደሚሆን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ለዚህም በዋናነት የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ ግብርና ወሳኙን ሚና እንደሚጫወቱና በተጨማሪም በግል ባለሀብቱ የሚካሄደው የሆርቲካልቸርና የሰፋፊ እርሻዎች ልማቶችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡ የአርሶ አደሩን የግብርና ልማት ለማፋጠን ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ለሁሉም አርሶ አደሮች ለማዳረስ፣ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የመስኖ ልማት ለማካሄድ እንደዚሁም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገኙ የግብርና ምርቶች ወደ ማምረት ለማሸጋገር ስልት ተነድፎ ርብርብ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ባለፉት ዓመታት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ፈጣንና ዘላቂ የግብርና ልማት ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ሌላው በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከተቀመጠው ግብ በላይ የላቀ አፈፃፀም የታየበት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የውሃ፣ የአፈርና የሥነ-ሕይወታዊ ሀብትን የሚያጐለብቱ የማህበረሰብ የተፋሰስ ልማቶች በዕቅድ ከተያዘው በላይ ተከናውነዋል፡፡

የተጐዱ አካባቢዎችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እንዲያገግሙ ተከልለው ጥበቃና እንክብካቤ ተደርጐላቸዋል፡፡ የአፈር መከላትን የሚከላከሉና የውሃ ሥርገትን የሚያጐለብቱ የማህበረሰብ ተፋሰስ የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ከዕቅድ በላይ ተከናውነዋል፡፡ በዚህም መሠረት እንዲያገግም የተከለለ የመሬት መጠን በዕቅዱ የመነሻ ዓመት ከነበረበት 3.2 ሚሊዮን ሄክታር ወደ 10.9 ሚሊዮን ሄክታር አድጓል፡፡ የማህበረሰብ ተፋሰስ መሠረተ-ልማት ግንባታ ወደ 20.2 ሚሊዮን ሄክታር ማድረስ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፍ በየዓመቱ በአማካይ 20 በመቶ አድጓል፡፡ ከታቀደው የዕድገት ምጣኔ አኳያ የተሳካ ዕድገት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመካከለኛና ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪ 19.2 በመቶ እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ 4.1 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት አስመዝግበዋል፡፡

በዚህ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ስኬታማ ከነበሩ ተግባራት ውስጥ የመሠረተ ልማት ሥራ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተለይ በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ ባለፉት 27 ዓመታት የተመዘገበው ስኬት በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጠቅላላ የፌዴራልና የክልል መንገዶችን በ2002 ከነበረበት 48 ሺህ 800 ኪ.ሜ በ2007 ወደ 63 ሺህ 604 ኪ.ሜ ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ 46 ሺህ 810 ኪ.ሜ የወረዳ መንገዶችም ተሠርተዋል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ጠቅላላ የመንገድ ርዝመት በ2007 መጨረሻ ወደ 110 ሺህ 414 ኪ.ሜ ደርሷል፡፡ በዚህም ወደ 76 በመቶ የሚጠጉ የአገሪቱ የገጠር ቀበሌዎች ክረምት ከበጋ በሚያስኬዱ መንገዶች እንዲገናኙ የተደረገ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ክረምት ከበጋ የሚያስኬዱ መንገዶች ላይ ለመድረስ የሚወስደውን ጊዜ በ2002 ከነበረበት 3.7 ሰዓት በ2007 ወደ 1.7 ሰዓት ዝቅ ሊል ችሏል፡፡

ሌላው ደግሞ የባቡር መሠረተ ልማት ነው፡፡ ከነበረው የዝግጅት እና የፋይናንስ አቅም ማነስ አንፃር ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው ርብርብ የተደረገባቸው የአዲስ አበባ-ጅቡቲ መስመር እና የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር መሥመር ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶችም ተጠናቀው ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ የአዋሽ- ወልዲያና መቀሌ-ወልዲያ-ሃራገበያ መስመ ሮችም ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያቃልሉ ይጠበቃል፡፡

በሀገራችን ፈጣንና ዘላቂ ልማት ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ጠቅላላ የኃይል ማመንጨት አቅምን በ2002 ከነበረበት 2000 ሜጋ .ዋት በ2007 ወደ 8,000 ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዶ 4,180 ሜጋ ዋት ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህንን ዕቅድ ተፈፃሚ ከማድረግ አኳያ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋና መለያ የሆኑት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የትምህርት ዘርፍ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ ትኩረት ከተሰጣቸውና በስኬት ከተከናወኑ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ምንም እንኳን በትምህርት ጥራት ላይ የሚጠበቀው ውጤት ማምጣት ላይ ገና ብዙ መጓዝ የሚጠይቅ ቢሆንም ተደራሽነቱን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ግን ስኬታማ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት በዘርፉ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ የአገራችን ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ አስችሏል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ከ27 ዓመታት በፊት አንድ ብቻ የነበረውን የዩኒቨርሲቲ ቁጥር ከ50 በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ አመርቂ ውጤት ከተመዘገበባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ደግሞ የጤናው ዘርፍ ነው፡፡ በዘርፉ የምዕተ ዓመቱን ግቦች ቀድሞ በማሳካት ረገድ ተጠቃሽ ምሳሌ እየሆነች ትገኛለች፡፡ የመሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ እንዲቻል በስታንዳርዱ መሠረት ጤና ኬላዎችና ጤና ጣቢያዎች በሁሉም አካባቢዎች ተገንብተዋል፡፡

በዚህም መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋንን በ2007 ወደ 98 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ የእናቶችንና የሕፃናትን ጤና ከማሻሻልም አንፃር ዕድሜያቸው አምስት ዓመት ሳይሞላቸው የሚሞቱ ሕፃናት ቁጥር በ1982 ከነበረበት 20ነጥብ 4 በ2007 ወደ 6ነጥብ 4 ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ የእናቶች ሞት ምጣኔ በ1982 ከነበረበት 1 ነጥብ 4 በ2007 ወደ 0 ነጥብ 42 ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የሀገራችንን የትራንስ ፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ የሚያፋጥኑ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በዕቅዱ የትግበራ ሂደት ቁልፍ በሆኑ ሀገራዊ የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከሀገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ ከፍተኛ ሕዝባዊ መነሳሳትና የጋራ የልማት መንፈስ የተፈጠረበት እንደነበርም ታይቷል፡፡

ኅብረተሰቡን በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በየደረጃው በማሳተፍ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በማህበራዊ ልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከተመዘገቡ ስኬቶች እና በጅምር ላይ ካሉ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያ ህዳሴ ዕውን ሊሆን የሚችል አጀንዳ መሆኑን ያየንበት ነው፡፡ ይህ ስኬት ደግሞ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመንም ተጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል፡፡ እነዚህ ደግሞ የግንቦት 20 ትሩፋቶች ናቸው፡፡
(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ) ውቤ ከልደታ

No comments:

Post a Comment