Sunday, December 17, 2017

የፌዴራል ሥርዓቱን ልንንከባከበው ይገባል

(Dec 17, (ርዕሰ አንቀፅ))--‹‹በአገራችን ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የፌዴራል ሥርዓት ሁሉንም የአገሪቱን ሕዝቦች በእኩልነት ላይ በተመሰረተና በተገነባ፤ ማንነታቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና እምነታቸውን ባስከበረበት፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድ ሩበት፣ በክልላቸው በሙሉ ነጻነት የሚሰሩበት ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ የሁሉም ክልሎች አጠቃላይ ድምር ውጤት ሲሆን፤ በአገራችን የዜግነት መንፈስ በሁሉም ሕዝቦች አንድነትና አብሮነት የጋራ አገራዊ ጥንካሬ በጸና መሰረት ላይ የታነጸበትና የቆመበት ነው፡፡

በአገራችን የፌዴራል ሥርዓቱ ከተገነባ ወዲህ ሰላምን መሰረት ያደረገ እጅግ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት እድገት ተመዝግቧል፡፡ በክልሎችም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገቡት ስርነቀል መሰረታዊ ለውጦች ሊደረስባቸው የቻሉት አገሪቱ የተረጋጋ ሰላም ስለነበራት ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት አገራዊ ልማትና ዕድገት ሊገኝና ሊጎለብት የሚችለው ደግሞ አገር ሰላም ሲሆን ነው፡፡ ሕዝቡ ተጠቃሚ የሚሆነው በሀገር ላይ የተረጋጋ ሰላም ሲኖር ብቻም መሆኑን ማንም ይረዳል። ለዚህም ነው ሕዝቡ ከምንምና ማንም በፊት ቅድሚያ ለአገራዊ ሰላም መጠበቅ የሚሰጠው።

በኢኮኖሚ በመሰረተ ልማት፣ በኮንስትራክሽን ፣በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በትምህርት፣ በጤናው በከተሞች መስፋፋት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችና ግዙፍ ግድቦችን መስራትና የመሳሰሉት መገኘት የተጀመሩት በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች የሚታዩት ተጨባጭ ድሎችና አመርቂ ውጤቶች ከረጅም ዘመናት ጦርነት የተላቀቁት አገሪቱ ሰፊ ሰላም ስላገኘችና የፌዴራል ሥርዓቱ መረጋገጥ ስለቻለ ነው።

እውቅና ያገኙት የመጻፍ፣ የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቶች ዜጎች በነጻነት በአገራቸው ላይ የመብታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ያረጋገጡትም እንዲሁ በሕገ መንግሥቱ መብታቸው ስለተከበረ ነው። ቀደም ባሉት መንግሥታት ይህን የመሰለው ሰብዓዊ መብት በሕገመንግሥት ደረጃ ተከብሮ አያውቅም። በሀገራችን በተፈጠረው አመቺ የመድብለ ፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓት በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕልውና አግኝተው በህጋዊነት ተመዝግበው በሀገሪቱ መንቀሳቀስ የቻሉትም በዚሁ የፌዴራል ሥርዓቱ ባመጣው ውጤት ነው። የአመለካከት ብዝሀነት፣ የአስተሳሰብ ነጻነት፣ ሁሉም ዓይነት አስተሳሰቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበት፣ የሚወከሉበት ሥርዓት መመስረትና መገንባት የተቻለ ቢሆንም መሰረቱን አጥብቆ፣ በተጨባጭ የታዩ ድክመቶችን እያረሙ መለወጥና መራመድን ይጠይቃል፡፡ በእርግጥ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀሩ በአገራችን ታሪክ ገና አዲስ የመሆኑን ያህል እንዲሰርጽ ለማድረግ ረጅም ርቀት ሄዶ መስራት ይጠበቃል።

ይህንን በውል ባለመረዳት ፌዴራሊዝሙን በተሳሳተ አቅጣጫ የሚተረጉሙት ወገኖች ብዝሀነትንና የሕዝቦችን መሰረታዊ ዴሞክራሲዊ መብቶችን ካለማክበር፤ መብቶችን ጨፍልቆ ልዩነቶችን ረግጦ የተወሰኑ ክፍሎችን የበላይነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ሲሉ የሚያራምዱት ሃሳብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ዴሞክራሲ ሰብዓዊና ተፈጥሯዊ መብት ሆኖ ሁሉም ዜጎች መብት ግዴታና ኃላፊነታቸውን በውል ተረድተው የሚጠቀሙበት፤ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ የሚጎናጸፈው መብት መሆኑ ቢታወቅም ወደ ተግባር ሲለወጥ ሰፊ ተግዳሮቶች ይኖሩታል፡፡

በተለይም የበለጠ የሚከፋው በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሕዝብና መንግሥት አምኖአቸው ይሰራሉ፤ ያገለግላሉ ተብለው የሚታመንባቸው ሰዎች ፀረ ዴሞክራሲና አምባገነናዊ አቋም ይዘው በሕዝብ ላይ መንገላታትና የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥሩ ሕዝብም ምሬት ውስጥ ገብቶ ሲታይ ጉዳዩን በስፋት በማጤን በመገምገም ሕዝብን ማዕከል ያደረገ መፍትሔ ማምጣት ግድ ይላል፤ እየተደረገ ያለውም ይሄው ነው፡፡

አንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚለው የዴሞክራሲ መርህ ዜጎች በክልልና በብሔራዊ ምርጫ ወቅቶች ይሰራልናል፤ ያገለግለናል የሚሉትን ተወካያቸውን ሲመርጡ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የአንድ ድርጅት ወይንም ፓርቲ የበላይነት ብቻ የሰፈነበት ሥርዓት ነው የሚለውን አካሄድ ለመቀየር የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ የግል ተወዳዳሪዎች ወደፓርላማ የሚገቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ድርድር ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት ፓርላማ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ዴሞክራሲያችን ታዳጊ ዴሞክራሲ በመሆኑ ረጅም ርቀት ሄዶ መስራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በበቂ ሁኔታ የዴሞክራሲ ምንነት ተገቢ መረዳት በአብዛኛው ዘንድ አልተንሰራፋም። ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት በየደረጃው ሊያድግና በትውልድና በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚሰፋ እንጂ በአንድ ጊዜ የሚደረስበት ባለመሆኑ ከነችግሮቹ ዴሞክራሲውን በተለያየ ደረጃ የማስፋቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ይታመናል፡፡

የዴሞክራሲውን ሂደት የማስፋቱና የማሳደጉ ሥራ በሂደት የሚቀጥል መሆኑን የምንረዳው ደግሞ ሥራው በአንድ ጀምበርና በጥቂት ዓመታት የሚደረስበት ስላልሆነ በዴሞክራሲ የጎለበቱና ያደጉ ሀገራት ዴሞክራሲ መገንባቱን ሥራ ለብዙ መቶ ዓመታት የተጓዙበት ከስህተትና ከውድቀታቸው እየተማሩ የበለጠ ለመስራት የሄዱበትን ረጅም ርቀት ምስክር ነው። እንቅፋቶችንና ተግዳሮቶችን እየተሻገረ፣ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እያስገኘ፣ በእውቀትና በትምህርት የሚሄድ ዴሞክራሲን መገንባት ለሀገር ልማትና ዕድገት የበለጠ ይበጃል፡፡

ሰፊ ግንዛቤ የመፍጠር፣ አቅምን የማሳደግ፣ የማብቃት ሥራን የሚጠይቅ ስለሆነም በፌዴራሉ ሥርዓት የተጀመረው ጅምር ይበልጥ እያደገ፣ እየበረታ ሊሄድ የሚችለው የመብቱና የስልጣኑ ባለቤት በሆነው በራሱ በሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝቡ መብቱን ግዴታውን አውቆ በአካባቢውም ሆነ በክልሉ አልፎም በፌዴራል ደረጃ ሀገራዊ አስተዋጽኦና ተሳትፎውን ሲያሳድግ ዛሬ ላይ እየታየ እንዳለው ጠያቂና ሞጋች ሕብረተሰብ ይበልጥ እየተፈጠረ ይሄዳል። ዴሞክራሲውም ሊያድግና ሊሰፋ የሚችለው በዚሁ መልኩ ነው፡

የተሰጣቸውን የሕዝብ ውክልና በመጠቀም ለሕዝቡ ከመስራትና ከማገልገል ይልቅ ራሳቸውን ሲጠቅሙ፣ በሕዝብ ሀብትና ንብረት ዘረፋ ኪሳቸውን ሲያደልቡ፤ ዘመድ አዝማዳቸውን ሲጠቅሙና የመሬትና የቦታ ባለቤት ሲያደርጉ የኖሩ፤ ሕዝቡን በፍትህ እጦትና በመልካም አስተዳደር ችግር እንዲበደል እንዲማረር ያደረጉና ሲያደርጉ የኖሩት ግለሰቦች ሕዝቡ በፌዴራል አወቃቀሩና በሥርዓቱ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር አድርገዋል፡፡ ዛሬ ላይ ፈተና ሆኖ የቀረበውም ችግር ይሄው ነው፡፡ እነዚሁ ወገኖች የፈጸሙት ሕገወጥ ድርጊት ሕዝቡ የፌዴራል ሥርዓትን እንዲያማርር፣ እምነት እንዲያጣና የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ይህ ማለት ፌዴራል ሥርዓቱ የፈጠረው ችግር ሳይሆን ግለሰቦች ሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ ሲያደርጉ የቆዩት አፍራሽ አሰራሮች ውጤት ነው፡፡

ለማስተካከል የሚሰራው ሥራ ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም በሂደት ለውጥ ማምጣት አይገድም፡፡ አሁን እየታየ ያለው ችግር የፌዴራል ሥርዓቱ ሳይሆን በሥርዓቱ ውስጥ መሽገው ተጠልለው በሥርዓቱ ላይ ሲዘምቱ የነበሩ ሰዎች ያስከተሉት ውጤት ነውና ይሄንን ለማረምና ለማስተካከል ነው በየደረጃው ሰፊ ሥራዎች በመሰራት ላይ ያሉትም። ዜጎች በሕገመንግሥቱ የተጎናጸፉትን መሰረታዊ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሕግ የተከበሩ በመሆኑ ሕግ በመተላለፍ የሚደርሱ ጥሰቶችን ታግሎ የማስከበሩ ኃላፊነት የሕዝቡ ነው፡፡በዚህ ረገድ የተከሰቱ በርካታ ችግሮች መታየታቸውን መካድ አይቻልም፡፡

በሕገ-መንግሥቱ የተረጋገጡት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተከብረው ሥራ ላይ እንዲውሉ በየደረጃው መታገል፤ ስህተቶች እንዲታረሙ መስራት፤ ተገቢ ያልሆኑ አሰራሮችን ማጋለጥ የሕዝቡ ኃላፊነት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በእርግጥ በየቦታው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨትና ለማናከስ ጥረት የሚያደርጉት ክፍሎች ይዘውት የተነሱት አላማ አንዱን ጎሳ በአንዱ ላይ እንዲነሳ በማድረግ የሀገሪቱን ልማት ዕድገትና የተረጋጋ ሰላም የማደፍረስ፤ ወደኋላ የመጎተት ሥራ በመሆኑ ሕዝቡ በያለበት ተግቶ እየታገላቸው ይገኛል፡፡ ይሄው እንቅስቃሴያቸው የሚደገፈው የሀገሪቱን ሰላም በማይመኙ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ጭምር ቢሆንም ታትረው ግን መጋፈጡን መዘንጋት የለባቸውም።

የተፈጠሩትን ችግሮች በሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው። ቀደም ሲል የተሰሩት ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋልም። ወደፊትም ይሄው የጋራ መተሳሰብና ተግባቦት በበለጠ ደረጃ እየተጠናከረ ጎልብቶ መቀጠል አለበት፡፡ በእነዚህ ረጅም ሂደቶች ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በዘለቄታው ለማስወገድ የሚያስችል ተሞክሮ በፌዴራላዊው ሥርዓቱ መዳበር ችሎአል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ የበለጠ ሕዝቦችን ለማስተሳሰር፣ ለማቀራረብና ለማግባባት ያስቻለ ከመሆኑም በላይ በየዓመቱ እለቱ የሚከበርበት ክልል ከሌሎች ክልሎች ልምድና ተሞክሮ በማግኘት በመማር አዳዲስ የልማት ሥራዎች የሚሰራበት ዕድገትና ለውጥም የሚያስመዘግብበትን ሁኔታ ፈጥሮአል፡፡ አንዱ ሌላውን ለማወቅ ባህሉን ለመረዳት፣ የበለጠ ለመቀራረብም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በዓሉን በድምቀት ለማክበር ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በየዓመቱ መካሄዳቸውና ግንባታዎቹ የክልሉን ዕድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑም ሌላው የበዓሉ መልካም ገፅታ ነው። ይህ ሁሉ የፌዴራል ሥርዓቱ ትሩፋት መሆኑ ደግሞ አይካድም፤ በመሆኑም፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ልንንከባከበው እንጂ ልናጎሳቁለው አይገባም።
ዋኘው መዝገቡ (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
 

No comments:

Post a Comment