Tuesday, December 19, 2017

ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ምን ነካቸው?

(Dec 19, (ርዕሰ አንቀፅ))--በየትኛውም አለም የሚገኙ የኒቨርሲቲዎች የጥናትና የምርምር ማዕከል የጥልቅ እውቀት መገብያ መምህራንና ተማሪዎች ለአንድና አንድ አላማ ብቻ የሚገናኙበት የእውቀት ማዕድ የሚገበዩበት ተቋሞች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ የእውቀት ልህቀት ማዕከል ከመሆኑም ባሻገር የነገ አገር ተረካቢ መሪዎችን የሚያፈራ ማሕጸንም ነው፡፡

ይህ ተቋም የአገሪቱ የነገ ተስፋዎች በጥልቅ እውቀት ተኮትኩተው የሚያድጉበት፥የህዝብ ልጆች ለፍተው በተማሩት እውቀት ለአገር የሚበጅ ታላቅ ስራ የሚሰሩበትም ጭምር ነው፡፡ ሁሉም ዜጎች በተቋሙ ያለልዩነት አብረው ኖረው፤ ተምረው ፍቅርና ወንድማማችነትን አሳድገው የእውቀት ማዕድ የሚቃመሱበት እንደሆነም ይታወቃል፡፡

ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ትምህርት ጨርሰው ሲመረቁም በግቢው ቆይታቸው በመሰረቱት ትውውቅ እስከ ወዲያኛው ወዳጅነት መስርተው የሚገናኙበት ታላቅ መድረክም ነው፡፡ አሁን አሁን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚስተዋለው ነገር ለመስማት የሚያስፈራንና ለማመንም የሚከብድም ጉዳይ ሆኗል፡፡ የእውቀትና የልህቀት ማዕከሎቻችን ወደዚህ የዘቀጠ ደረጃ ምን አወረዳቸው? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ዩኒቨርሲ ቲዎቻችንን ምን ነካቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት የወደድኩት፡፡

እንደ አገርም እንደ ሕዝብም ቆም ብለን ማሰብ የሚገባንም ጊዜ ነው፡፡ ይህ ክፉ ደዌ የሆነው የጎጠኝነት ካንሰር በሽታ በጊዜው ሊታከም ካልቻለና መፍትሄ ካላገኘ መዘዙ መቋጫ የለውም፡፡ አደጋው ለአገር ይተርፋል፡፡ ከወዲሁ መላ ልናበጅለት አንድ ልንለውም ይገባል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የመማር ማስተማሩ ሂደት በስርዓቱ የሚከወንባቸው የእውቀት አዝመራ የሚገበይባቸው አውድማዎች ናቸው፡፡ እንደሌላው አለም ሁሉ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ቅጥር ግቢ ውስጥ ከመማርና ማስተማር ሂደቱ ውጭ የእርስ በእርስ ብጥብጥና መናቆሪያ ሜዳ እንዲሆኑ ማንም አይፈቅድም፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ የምርምር ሀሳቦች የሚፈልቁባቸው በየትኛውም በሚነሳ ሀሳብ ላይ ጥልቅ ምሁራዊ ውይይት የሀሳብ መንሸራሸር የሚካሄድባቸው በምክንያታዊነትና በአመክንዮ የሚያምን ትውልድ የሚፈጠርባቸውና የሚታነጽባቸው ናቸው፡፡

ነገ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደስራ ሲሰማሩ አገርና ሕዝብን በእውቀት ለማገልገል ዝግጁ የሆኑ ወጣቶችን የምናፈራበት በተግባርም ወደስራ ገብተው የሚያገለግሉ ከድሕነትና ከኃላቀርነት ለመውጣት በሚደረገው እልህ አስጨራሽ በፈተና የተሞላ ትግልና አገራዊ ጉዞ የበኩላቸውን ታላቅ የዜግነት ግዴታ የሚወጡ ምሁራንን የምናፈራበት ነው፡፡

የቀደመው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የነበረው ትውልድ ለሀገር ለሕዝብ የሚበጅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ መንግስታዊ አስተዳደር በአገራችን እንዲመጣ ሲታገል የኖረ ነበር፡፡ ጎጠኝነትን የጎሳና የዘር ፖለቲካን በአያሌው የተጸየፈ ትውልድም ነበር፡፡

በፊውዳላዊ ስርዓት ውስጥ የኢትዮጵያ ገበሬ ከጭሰኝነት ከጉልበት ገባርነትና ባርነት እንዲወጣ አርሶአደሩ የመሬቱ ባለቤት እንዲሆን የሕዝብ ሀብቶች ለሕዝብ እንዲሆኑ፤ የሠራተኛው የጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም በሰራተኛ ማሕበራት በኩል ሠራተኛውን አደራጅቶ ለሕዝብ መብትና ጥቅም ሲታገል የነበረና ታላቅ የትውልድ መስዋእትነት የከፈለ ፋና ወጊ ነበር፡፡ እሳቤው ከጎጥና ከዘር የወጣ የእይታ አድማሱ ከብሔራዊ ደረጃ አልፎ አለም አቀፋዊ ነበር፡፡ ዛሬ እንደ ትንግርት እንደምንሰማው ቁልቁል ወርዶ የተፍገመገመ ወደ መንደርና ቀበሌ የወረደ አልነበረም፡፡

የመሬት ላራሹ ጥያቄ የቀደመው ትውልድ ተራማጅ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ጥያቄ ነበር፡፡ የዛን ጊዜው የዩኒቨርስቲ ተማሪ በሁሉም መስፈርት ሲታይ የላቀ አገራዊ እሳቤ ባለቤት የነበረ፤ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ሰብአዊ ነጻነቱ ዴሞክራሲያዊ የመናገር የመጻፍ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ የመደራጀት መብቶች እንዲከበሩ በጽኑ የታገለ ለዚህም የሞተ የቆሰለ የተሰደደ ነበር፡፡

የትግል አርማው አድርጎ ይወስዳቸው የነበሩት አለም አቀፍ ታጋዮችን የግራ ዘመም ማርክሳዊ ርእዮተ አለም መሪዎችንና ቀደምት ተጠቃሽ ምሳሌዎችን ነበር፡፡ ለምሳሌም የቻይናውን አብዮት መሪ ማኦ ዜዱንግን የቪየትናሙን ሆቺሚኒን፤ የሩሲያውን የጥቅምት አብዮት መሪ ብላድሚር ኤሊይች ሌኒንን፤ የአፍጋኒስታኑን ሀምበር ሆጃን፤ የኩባውን ፊደል ካስትሮን፤ የደቡብ አፍሪካውን ከአፓርታይድ ነጻ ለመውጣት የታገለውንና 30 አመታት በእስር ቤት ያሳለፈውን የአፍሪካ ኮንግረስ መሪ የነበረውን ኔልሰን ማንዴላን መጥቅስ ይቻላል፡፡ ድንበር ዘለል አለም አቀፋዊ እይታና ሰፊ ግንዛቤ የነበረው ትውልድ ሆኖ አልፏል፡፡

ይህ ማለት ስርነቀል አብዮትን ያቀነቅን የነበረው ኢትዮጵያዊው የዩኒቨርስቲ ተማሪ ከብሔራዊ ደረጃ ያለፈ ከዘር ከጎጥ ከመንደር አስተሳሰብ እጅግ መጥቆ የራቀና ከፍ ብሎ በብሔራዊ በአህጉራዊ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ የታነጸና የተቀረጸ አስተሳሰብ አራማጅ ተሟጋች ተከራካሪ የነበረ ነው፡፡

የቀደመው ዘመን የዩኒቨርስቲ ተማሪ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲዊ ስርአት እንዲገነባ፤ በሕዝብ በሚመረጥ የሕዝብን ይሁንታ ባገኘ መንግስት መተዳደር አለባት፤ የመንግስት ስልጣን ከምርጫ ድምጽ ብቻ መመንጨት አለበት፤ ቤተሰባዊ የሆነ ንጉሳዊና መሳፍንታዊ አገዛዝና አስተዳደር ሰፊ ለሆነችው ሀገር አይመጥንም፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መብት በእኩልነት የተከበረባት የሁሉንም ዜጎችዋን መብትና ነጻነት ባሕል ቋንቋን እምነት ያለአድልዎ በእኩልነት ያከበረች፤ ልዩነቶችን አቻችላ በጋራ በነጻነት ሁሉም በዜግነቱ ኮርቶና ታምኖ የሚኖርባት ኢትዮጵያ መፈጠር አለባት በሚል ነበር መራራ ትግል ያደረገው፡፡

ወቅትና ዘመኑ ቢርቅ ታሪክ ቢቀያየር ሁኔታዎች ቢለዋወጡም ይሄንን የሕይወት ምስክርነት ሊሰጡ የሚችሉ በርካታ ታላላቅ ኢትዮጵያውን በአገር ውስጥም በውጭም ዛሬም አሉ፡፡ ዛሬ በዩኒቨርስ ቲዎቻችን ያሉ ተማሪዎቻችን የቀደሙት አባቶቻቸውን ፈለግ ተከትለው ስለአገር ትልቅነት ስለሰው ልጅ በእኩልነት የመኖር የመስራት የመማር የተከበረ ነጻነት ማሰብ ከሚገባቸው ደረጃ ወርደዋል፡፡

በጎሳ፤ በዘር እየተቧደኑ መጋጨቱን፤ መሰዳደቡን፤ ቡድን ፈጥረው መጣላቱን መደባደቡን፤ የአካል ጉዳት ከማድረስ እስከ ተማሪዎች ሕልፈተ ሕይወት ድረስ የዘለቁ አሰቃቂና አሳዛኝ እንዲሁም በማንኛውም ኢትዮጵያዊ አይን ሲታይ በእጅጉ አሳፈሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ፡፡ ይህ የቀደመውን መነሻ ሙሉ በሙሉ የሻረና የደመሰሰ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ከጎሳና ከዘር አስተሳሰብ በላይ የመጠቀና የረበበ ነው፡፡ የመጀመሪያው የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ እንደምሆንዋ መጠን አለምን ተራብቶ የሞላት ኢትዮጵያዊ መሆኑ ይታመናል፡፡ እንኳን እኛ ቁልቁል ወርደን በጎሳና በዘር ልንናቆር ቀርቶ መልክዓምድርና የአየር ንብረት ቀለሙንና ቋንቋውን ኑሮውን ባሕሉን ወዘተ ቢለውጠውም መላው አለም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ትልቅ ነበርን፤ትልቅም ነን፤ ትልቅም እንሆናለን፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የሰላምና የትምሕርት ማዕከላት እንጂ መለስተኛ ጦር ሜዳ ሁነው ወንድም ወንድሙን የገዛ ወገኑን የሚጎዳባቸው፣ የሚያቆስልባቸውና የሚገድልባቸው አካባቢዬን ለቃችሁ ውጡ የሚባልባቸው አይደሉም፤ሊሆኑም አይችሉም፡፡ እንዲህ አይነት የወደቀ አስተሳሰብ ያውም በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ በኢትዮጵያ ምድር ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ባለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ ትምሕርቱን በሰላም የመማር ሙሉ መብት አለው፡፡ ሰሜን ሆነ ደቡብ ምስራቅ ሆነ ምእራብ መሀል አገር ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ነች፡፡ አገሩ ነች፡፡ እናት መሬቱ ነች፡፡

ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የትኛው ክፍል በተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብተው ሳይፈሩ፣ ሳይጨነቁና ሳይረበሹ በሰላም የመማር መብታቸው በሙሉ ነጻነት የተከበረ ነው፡፡ አገራዊና ሕዝባዊ ተስፋ ከተጣለበት ሀገርን ሊለውጥና ሊያለማ ሊያሳድግ ይችላል ተብሎ ከሚታመነበት የእውቀት ማእከል በማይጠበቅ ለማመንም በሚያስቸግር የጎሳ ፖለቲካን በማቀንቀን መናቆር መጋጨት አሳፋሪም አሳዛኝም ነው፡፡ ድሮም እኮ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች በየትኛውም የአገሪቱ የትምህርት ተቋም ውስጥ አብረው ነው በፍቅር ኖረው የተማሩት፡፡ ዛሬ አዲስ የተፈጠረው ነገር ምንድነው ነው ጥያቄው፡፡

ኢትዮጵያ እንኳን የራስዋን ልጆች ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተማሪዎችን እየተቀበለች የምታስተምር የምታኖር ለቁም ነገር አብቅታ አስመርቃ የምትሸኝ አገር ነች፡፡ በዚህ ደረጃ ሲታይ ጊዜ ወለድ የሆነውን የጎሳና የዘር ልክፍት በሽታ ጎጠኝነትንና መንደርተኝት እስከወዲያኛው ልንጠየፈው ልንዋጋው ይገባል፡፡ ለዛሬውም ለቀጣዩም ትውልድ አይበጅም፡፡ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች የአስተሳሰብ ድሆች ከሰውነት ደረጃም በታች ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ አብሮነት አይበጁም፡፡ እንዲያውም በአገርና በሕዝብ ላይ ታላቅ ውድቀትን ያስከትላሉ፡፡

የሰው ልጅ ሁሉ ሰው ሁኖ በመፈጠሩ እኩል ነው፡፡ ቅዱስ መጻህፍትም እንዳስቀመጡት በእውቀት በሀብት በክህሎት በኢኮኖሚ በማሕበራዊ ደረጃ ወዘተ ሊለያይ ይችላል፡፡ይሄ ያለ የነበርም ነው፡ ነገር ግን አንተ የእከሌ ጎሳ ነህ ከዚህ ለቀህ ውጣ ሂድ፤ አንተ ከዚህ ዘር ነህ አካባቢያችን ልቀቅ፤ድብደባ ውግዘት የአካል ጉዳት መፍጠር መግደል በአገርና በሕዝብ ላይ ትልቅ አደጋና ችግር ያስከትላል፡፡ መርዘኛ አስተሳሰብም ነው፡፡ ሕዝብ በአንድነት ቆሞ ሊከላከለው ግድ ይላል፡፡ መጨረሻው ምንድነው? የሚለውንም አርቆ ማሰብ ይጠይቃል፡፡

አባት እናት ልጁ በተመደበበት ቦታ ሄዶ እንዲማር የሚልኩት አገሩ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ህግንና ስርዓት ያለባት አገር ናት ብለው ስለሚገነዘቡም ጭምር፡፡ ማንም ወላጅ ልጁ እንዲጎዳ እንዲንገላታ እንዲደበደብም ሆነ እንዲሞት አይፈቅድም፡፡ እንደ አገር ስናይ የተፈጸመውም ሆነ የሆነው ነገር አሳፋሪ ነው፡፡

ይሄንን ቁማር ሆን ብለው ከጀርባ የሚጫወቱት የሩቅና የውስጥ ስውር እጆች የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት በፍጹም ማየት የማይፈልጉ፤ ሰላም እንዲደፈርስ ሕዝብ ከሕዝብ እንዲጋጭ፤ በዚህም ሀገሪቱ የማትወጣበት የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትገባ በስተመጨረሻም ኢትዮጵያ ልክ እንደ ሊቢያ ሶርያ የመን እንድትበታታንና እንድትፈራርስ የሚፈልጉ ቅጥረኞች ናቸው፡፡ ይሄን የቤት ስራ በዋነኛነት ይዘው በብዙ ሚሊዮኖች ዶላር ተመድቦላቸው ኢትዮጵያዊ መስለው ኢትዮጵያውያንን የሚያባሉ የሚያፋጁ በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ የውስጥ አርበኞች የሚጫወቱት መርዘኛ ጨዋታ ነው፡፡ ተማሪዎቻችን ይሄንን እውነት ካላወቁት ሊያውቁት ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ ከዚህ አይነቱ የእብደት ስራ ሊታቀቡም ይገባል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ትምህርት ለመማር በአንድ ካምፓስ ሲሰባሰቡ መኖር የሚገባቸው በፍቅር በመተሳሰብ በአብሮነትና በመቻቻል ነው፡፡ ተማሪዎቹ በሙሉ እከሌና እነ እከሌ ሳይባሉ ሳይባባሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች ናቸው፡፡ በጎሳ በጎጥ በቡድን እየተከፋፈሉ በጠላትነት የሚተያዩበት ምእራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መዘጋት አለበት፡፡ ያለስጋት ያለጭንቀት ተምረው ትምህርታቸውን ጨርሰው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልግል የሚዘጋጁ መሆን ነው ያለባቸው፡፡

ይህንን በእነሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአገር ላይ የተቃጣ ሕዝብን የመከፋፈልና የውጭ ኃይሎች እጅ ያለበት ስውር ሴራ ተረድተው በጣጥሰው በመጣል ፍቅርና ወንድማማችነትን ማጎልበት መተዛዘን መረዳዳት በጋራና በሕብረት ጸንተው መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡

እንዲህ አይነቱ ነውረኛ ድርጊት አገርና ሕዝብ በታላቅ የነገ ተስፋ ከሚጠብቃቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በፍጹም አይጠበቅም፡፡ ማንኛውም ተማሪ በጎሳውና በዘሩ ምክንያት የጥቃት ሰለባ ሊሆን አይገባም፡፡ከዚህ አደገኛ አዙሪት ፈጥኖ ለመውጣት ሁሉም ቅንና አገር ወዳድ ዜጋ በጋራም ሆነ በተናጠል የማረጋጋት ሁኔታውን ወደ ሰላማዊው መንገድ የመመለስ ስራን መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያና ለሕዝብዋ ይሁን !
መሐመድ አማን  (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

1 comment:

Thomas said...

you have to know that , the cause of the problem is the government.
the regime divide the country based on race and ethinicity through The federal arrangement. some Opposition groups and persons which live out side also responsible. They organized them selves through race and they
encourage young students to be racist and by providing false informtion. Generally in Ethiopia there was class based oppression but not racial oppression so, We have to know that the root of the problem is race based federalism ,and we have to cancel a constitutional recognition racial based oppression.

Post a Comment