Wednesday, November 08, 2017

«የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ»

( ጥቅምት 29, (አዲስ ዘመን, (ዜና ሐተታ)))--ጣና ሃይቅ ከታመመ ሰነባብቷል። አስታማሚ አጥቶ የእንቦጭ አረም ህልውናውን ተፈታትኖታል። ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ ከሃይቁ ሰፊ ቦታ በእንቦጭ አረም ተወሯል። በርካቶችን ስጋት ላይ በመጣሉም ሁሉም ባለው አቅም መፍትሄ ለመፈለግ ደፋ ቀና ማለቱን ተያይዞታል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከክልሉ ከተለያዩ ስፍራ የተውጣጡ ወጣቶች ጣናን የተፈታተነውን እንቦጭ በእጃቸው ለመመንገል ጥረት ሲያደርጉ ከርመዋል። ከኦሮሚያ ክልልም ከ200 ያላነሱ ወጣቶች ወደ ሥፍራው አቅንተው እንቦጭን ለማጥፋት የተቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ጣና ለመዝመት ያቀዱ ወጣቶችም እንዳሉ ይሰማል። ከዚህ ጥረት ባሻገር በአማራ ክልል የሚገኙ የሃይቁ አጎራባቾች የጎንደር እና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች የጣና አጋሮች ነን ሲሉ ዓይናቸውን በምርምር ላይ ተክለዋል።

የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፤ የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዘገባ በ2009 በጀት ዓመት ከ24ሺ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የእንቦጭ አረም ተከስቷል። በቀን ከ90ሺ በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ 19ሺ ሄክታር ላይ ያለውን አረም ማስወገድ መቻሉን ጠቅሷል። ጣና ሐይቅ የክልሉ ሐብት ብቻ ባለመሆኑ አረሙን በቅንጅት ለመከላከል የተደረገው ጥረት አናሳ መሆኑንና በተጨማሪም አረሙን ለመከላከል በክልሉ በኩል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁሟል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ እንደሚሉት፤ የጣና ጉዳይ አንገብጋቢ እና ለነገ የማይተው አጀንዳ ነው ይላሉ። እንቦጭ ከተከሰተ ጀምሮ በርካታ የምርምር ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የሰው ጉልበት የሚተካ ማሽን መፈብረክ አንዱ ነው። በኬሚካል ማጥፋት የሚያስችሉ ምርምሮች ተከናውነዋል። እንቦጭ አረምን ለሌላ ጥቅም ማዋልም ሌላኛው የመፍትሄ አካል እንደሚሆን ታስቦ ምርምር ሲደረግ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው ለሦስት አመታት ምርምር ያደረገበትን አዲስ ማሽን ይፋ አድርጓል። ሥራ ላይ የዋለው ማሽንም በዩ ኒቨርሲቲው ኢንጅነሪንግ ወርክሾፕ ውስጥ የተሰራና ረጅም ጊዜ ጥረት የተደረገበት ነው። የጣና ሀይቅ ባህር ትራንስፖርት ድርጅትም ማሽኑ በውሃ ላይ መንሳፈፍ መቻሉን ብሎም ሚዛኑን መጠበቅ እንደሚችል ማረጋገጡንና ለታለመለት ዓላማ ሊውል እንደሚችል ማረጋገጫ መስጠቱን ፕሮፌሰር መርሻ ተናግረዋል።

«የጎንደር መካነ አዕምሮ ፈጠራ ውጤት» የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ማሽን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያከናውናል። ለአብነት በዋናነት አረሙን ከሀይቁ ላይ ይሰበስባል። ከሰበሰበ በኋላም ወደ መፍጫ ክፍሉ ይልከዋል፤ ከተፈጨ በኋላ ወደ ውጭ ከ30 እስከ 40 ሜትር አርቆ መርጨት ይችላል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በዋናነት አረሙን ከሃይቁ ማስወገዱን እንጂ ሌላው ጥቅሙ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት ይሆናል። እንቦጭን ወደ አፈር ማዳበሪያ መቀየርና ለቤት መስሪያ የሚውሉ ፕሪካስት እና ብሎኬት የተሰኙ ግብዓቶችንም ለማምረትም ታስቧል።

ማሽኑ 10 ቶን የተፈጨ እንቦጭን መያዝ የሚችል ሲሆን በሂደት ሊሻሻል እንደሚችል ይጠበቃል። እስካሁንም ለማሽኑ ሥራ 3ነጥብ8 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። በብዛት በአገር ውስጥ ቁሳቁስ የተሰራ ነው። ከውጭ የሚገዛውን ማሽን ሊተካ እንደሚችልም ተናግረዋል። ዋናው ተመራማሪና የፕሮጀክቱ ባለቤት ኢንጅነር ሰለሞን መስፍን ሲሆኑ፤ በርካታ መምህራንና ከግቢው ውጭ የቴክኒክና ብየዳ ስራዎች ላይ የተሳተፉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል። የጣና ሀይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ሙያዊ እገዛ እያደረገ መሆኑን አስታውሰው ሥራው አገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ትርጉም እንደሚኖረው ጠቁመዋል። ማሽኑ በአሁኑ ሰዓት በነዳጅ የሚሰራ ሲሆን፤ በፀሃይ ሃይልም እንዲሰራ ዲዛይን የተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት የሚያግዝ ኬሚካል በምርምር አግኝቷል። የአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ባለበት በቤተ ሙከራ ተፈትሾ ውጤታማነቱ ተረጋግጧል። ሌሎች ኬሚካሎችም አሉ። ይሁንና በውሃ ውስጥ ያሉ እፅዋት እና እንስሳት ሊጎዳ ስለሚችልና በሀይቁ ላይ ስላልተሞከረ ወደ ግልጋሎት አልገባም። የባለቤትነት መብት ከተረጋገጠ በኋላም እስካአሁን ይፋ ያልተደረጉ ሁለት ግኝቶች በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ምርምሮች እንደሚደረጉ አረጋግጠዋል።

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ብሉ ናይል ወተር ኢንስቲትዩት ተማራማሪ እና በባዮሎጂ ዲፓርትመንት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ጌታቸው በነበሩ በበኩላቸው፤ የእንቦጭ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ወደ ምርምር በመገባቱ አረሙን ስልቅጥ አድርገው የሚበሉ ጢንዚዛዎችን እየተራቡ መሆኑን ይገልፃሉ።

የተራባው እጭ ወደ ውስጥ ገብቶ የአረሙን ስር የሚበላ ሲሆን፤ «አዳልቱ» ደግሞ ቅጠሉን ይመገባል። ይህን ወደ ተግባር ለማስገባትም የክልሉን እና ከፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ይሁንታ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ነው። ቀደም ሲልም መሰል ተግባራትን በዓለም ላይ 33 አገራት ሞክረውታል። ለአብነትም ከአፍሪካ በኬንያ ተሞክሯል። ጢንዚዛዎቹ ውሃ ውስጥ መራባት ይችላሉ። እነዚህም ከእንቦጭ ውጭ ሌሎችን እፅዋት የማይመገቡና አረሙ ሲያልቅባቸው ይሞታሉ፤ በመሆኑም ጉዳት እንደማያደርሱ መረጋገጡን ተናግረዋል።

ለመራባት 150 ጢንዚዛዎች ከወንጅ ስኳር ፋብሪካ የመጡ ሲሆን በአምስት ወራት በተደረገው የማራባት ስራ ከ2000 በላይ ደርሰዋል። ስራው ብዙ ብር ሳይሆን ብዙ ክትትል የሚያስፈልገው ነው። ሆኖም ጢንዚዛዎቹ ወደ ውሃ ገብተው አካባቢውን እስኪላመዱት ድረስ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ነው የሚጠቁሙት።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ እንቦጭ አረም በኢትዮጵያ ከ15 ዓመታት በፊት በቆቃ ወንዝ ላይ ተከስቶ ነበር። አሁንም ችግሩ እንዳለ እየተነገረ ነው። አረሙ እጅግ አደገኛና ከ8 እስከ 16 ቀናት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ራሱን በእጥፍ ያባዛል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር ((አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment