Thursday, November 02, 2017

ሚዲያው ለሰላምና ለሀገራዊ አንድነት ይቁም!

(ጥቅምት 24, (አዲስ ዘመን,  (አጀንዳ)))--ማህበራዊ ሚዲያው ባሕላዊ ሚዲያ ተብሎ ከሚጠራው ጋዜጣና መጽሔት እንዲሁም ከቴሌቪዥን እጅግ በፍጥነት በማደግና ታዳሚዎቹም በመስመር ላይ ሆነው በተጠንቀቅ የሚጠብቁት ሆኗል፡፡ ይህ ማህበራዊ ሚዲያ ለበርካታ አገልግሎቶች የመዋሉን ያህል እጅግ አደገኛ የጥፋት መሳሪያ በመሆኑ በኩል የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ዓለምአቀፍ አሸባሪዎች ማህበራዊ ሚዲያን በስፋት ተጠቅመ ውበታል፡፡ በአሰቃቂ ሁኔታ ሰዎች አንገታቸው ሲቀላ (ሲታረድ) የሚያሳዩ ፎቶዎችን በመልቀቅ ከባድ የሥነልቦና ጦርነት በማድረግ ረገድ ተልዕኳቸውን የተወጡት በዚሁ ሚዲያ አማካይነት ነው፡፡

ማህበራዊ ሚዲያው በቅጡ ካልተያዘ ሀገር ይፈርሳል፡፡ ሕዝብንም ከሕዝብ ያባላል፡፡ ታላቅ ጥፋትና ውድመትንም ያስከትላል፡፡ ይህን በቅርቡ በሌሎች አገሮች ማየት ችለናል። ይሁንና አንዳንዶች በሌላው ሀገር የተፈጸመን ሰቅጣጭ ግድያና ጭፍጨፋን የሚያሳዩ ፎቶዎች እየወሰዱ በፎቶሾፕም እየሰሩ ልክ እኛ ሀገር የተፈጸመ አድርገው የመዓት አውርድ መዓት አምጣ ተልዕኮን በማንገብ ሕብረተሰቡን የማሸበር፣ የማስቆጣት፣ የማነሳሳትና ጥፋት እንዲከሰት የማድረግ ሥራ ሆነ ብለው ሲሰሩ አስተውለናል፡፡ የዚህ ሁሉ ባለቤት ማህበራዊ ሚዲያው ነው፡፡ ይህ ግን አይጠቅመንም፤ አይበጀንምም፡፡

ከሰሞኑ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ ማህበራዊ ሚዲያው እጅግ አስፈሪና አሳፋሪ እየሆነ ነው። ሀገራዊ ጥፋትና እልቂት እንዲከሰት ቀን ከሌሊት ሲሰሩ በነበሩ ነውረኞች ሕዝብን ከህዝብ፣ ዘርን ከዘር ሲያበላልጡና ሲያንቋሽሹ ቆይተዋል። በዚሁ ሚዲያ መልካምን ነገር የሚያስተላልፉ እንዳሉ ሁሉ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት የሌላቸው ዋልጌዎችም በስፋት ተፈልፍለውበት ያልተገባ መልዕክት ሲያስተላልፉም ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ሲሰራ የነበረው የጥላቻ፣ የመናቆር፣ የመባላት እንዲሁም የእኩይና ጽንፈኛ አክራሪ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳ ነፍስ ዘርቶ እልቂትና ደም መፋሰስ በኢትዮጵያ እንዲከሰት የሚፈልግ ሰው ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ብሎ ለመናገር እጅግ ያስቸግራል፡፡

ከሕዝብ እልቂትና ከሀገር ጥፋት የሚገኝ ትርፍ የለም፤አይኖርምም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ከዚህ እኩይና የአንድን አገር ህዝብ የማባላት ድርጊቱ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ ችግርን ማባባስ ሳይሆን የችግሩን መፍትሔ በሰላማዊ መንገድ በማስገኘት በኩልም የበኩሉን ጤነኛ ድርሻ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ የጥፋትና የእልቂት ከበሮ ጠዋት ማታ ከመደለቅ መላቀቅ ይጠበቅበታል፡፡

ኢትዮጵያ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመከባበር ተምሳሌት ሆና በልማትና በዕድገትዋ ዘልቃና መጥቃ የምትቀጥል ሀገር እንጂ ጠላቶችዋ እንደሚመኙት አትጠፋም፤ አትወድቅም፤ አትበታተንም፡፡

ኢትዮጵያውያን ጥንትም ቢሆን በተለያየ ዘመን ከመጡብን ወራሪዎች ደምና አጥንታቸውን ገብረው የጠበቋት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ በተዘረጋው ሰፊና የተንጣለለ ግዛትዋ የነበሩት ልጆችዋ ናቸው፡፡ ዛሬም ወደፊትም የሚሆነው እንዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከራስዋም አልፎ ለአፍሪካ ነጻነትና ክብር የቆመችና የታገለች ታላቅ ሀገር ነች፡፡ ለአፍሪካውያን ነጻነት የበኩሏን ያበረከተች፣ ብርሃንና ቀንዲል ሆና የምትወሰድ ሀገር ነች፡፡ ስለዚህም እንኳን ለእራሳችን ሀገር ቀርቶ ለሌሎችም ተርፈን ኖረናል፡፡

የሀገርና የወገን ሰላም በተመረዘና ቀፎ ጭንቅላት ባላቸው ሰዎች የአመጽ ቅስቀሳ ሊናጋ አይገባውም፡፡ ሰላምና መከባበር ቀዳሚ አጀንዳችን መሆን አለበት፡፡ ሀገሬ ሰላምሽን ያብዛልሽ፡፡

ወንዞች ተራሮችሽ፣ አውድማና ማሳሽ፣ ደብርና መስጊዶችሽ ሰላም ውለው ሰላም ይደሩ፡፡ ልጆችሽ፣ አባቶችና እናቶች፣ አዛውንትና ሕጻናት ክፉ አይንካቸው፡፡ ውድቀትሽን፣ መጥፋትሽን የሚሹ ሁሉ እንደሚጠፉ በዘመናት ሂደት ያለፈው ታሪክሽ ደግሞ ደጋግሞ አሳይቶናልና በአንድነት ጸንትን ልንቆም ይገባል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው የመዓት አውርድ ከበሮውን ይዞ ለሀገር ጥፋት፣ ለሕዝብ እርስ በርስ መጋጨት በሚደልቅበት በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ክፉ አይንካሽ ልንል ይገባል። የተጋረጠውንም አደጋ ልናመክነው ግድ ይላል፡፡

አንድ ሰው ሲሞት ሲጎዳ ሰው በመሆኑ ወገናችን በመሆኑ ብቻ ልናዝንና ልንጸጸት ይገባል፡፡ የእከሌ ጎሳ የእከሊት ዘር የሚለው የማህበራዊ ሚዲያው ዘረኛ በሽታ አንዱን ከአንዱ ከማናቆር ውጪ ለማንም አይበጅም። በሀገር ደረጃ ትልቁ ችግራችን ድህነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ ደግሞ ገና ያልሰራንባት ትልቅና ሰፊ ሀገር ስላለን የተጀመረውን ልማትና ዕድገት ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።

ግብጽም ሆነች ኤርትራ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ በኢትዮጵያ መሬት እንዲከሰት ሲሰሩ የኖሩ ናቸው፡፡ዛሬም ከጀርባ ያሉት ዋና ተዋናዮች የሀገር ውስጡን ተላላኪ የሚገፉት እነሱው ናቸው፡፡ ችግሩን ከስሩ በመፍታት ሀገራችንን ከጥፋት መታደግና ሰላምዋን ማስከበር ያለብን እኛ ልጆችዋ ነን፡፡

በኢትዮጵያ ምድር የተፈጠሩ ልጆችዋ ሁሉ እኩል የዜግነት የመብት፣ የመስራትና የትም ተዘዋውሮ የመኖር እንዲሁም ሀብትና ንብረት የማፍራት መብት አላቸው፡፡ ይህ ጊዜ የወለደው ጥላቻን የሚያራግብ በሽታ መጥፋት አለበት። ማህበራዊ ሚዲያው ጥርሱን አግጥጦ ከተነሳበት የዘረኝነት መንፈስ፣ ዜጎችን የማናከስ አባዜ ካልወጣ መንግሥትና ሕዝብ በቀላሉ አያልፉትም፡፡

እጅግ የዘቀጡ፣ የወረዱ፣ ከሰብዓዊነት የተፋቱና በከፋ የዘረኝነት በሽታ የተለከፉ ሰዎች ያየንበት አሳፋሪ ዘመን ቢኖር አሁን ያለንበት ነው፡፡ ጎሳም ሆነ ብሔር አይሰደብም፤ አይዘለፍም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን ለጥፋት መጠቀሚያ መሳሪያ አድርገው ባልተጨበጠ ማስረጃ ሕዝብን ለማነሳሳት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ሕዝብ ታዝቧቸዋል፡፡ ጥፋት ያደረሱት የትም ሄዱ የትም ከሕግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡም ሊረዱ ይገባል።

ገና ለገና ግርግር በተነሳ በማለት ተደራጅቶ ለመዝረፍና ለመንጠቅ ገጀራና ጩቤ ታጥቆ የተቀመጠና የሚጠብቅ ነፍሰ በላ በየቦታው እንዳለ ግልጽ ነው። እስከአሁንም አንገቱን የደፋው ሕግና ሥርዓት እንዲሁም ፖሊስና መከላከያም ስላለ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሰላም ከደፈረሰ፣ ሕግና ሥርዓት ካልተከበረ የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ መሆንም ይከተላል፡፡ የሀገርን ሰላም መደፍረስ የሚጠብቅ ዘርፌ ነጥቄ እከብራለሁ ብሎ የሚያስብ ስንትና ስንት ማጅራት መቺ በየቦታው ተደራጅቶ እንዳለ ማስተዋልም ያሻል፡፡

ሰላም ከደፈረሰ ሰላምን በመመኘት ማምጣት አይቻልም፤ ለሰላም መኖር ተባባሪ መሆንን ይጠይቃል። ሰላም ከሌለ ቤቴ፣ ንብረቴ፣ ሚስቴ፣ ልጆቼ ማለትም አይታሰብም። የመን፣ ሊቢያንና ሌሎች በእርስ በርስ ግጭት የሚማቅቁ አገራትን ያየ በሰላም አይቀልድም፡፡ በሀገር ሰላም ቁማር አይቆምርም፡፡

ኢህአዴግ የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ የመልካም አስተዳደር የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስና እንዲሁም የፍትህ እጦት ችግር የፈጠረው ነው ትርምስና ሁከቱ፡፡ይሄንን ችግር ለመፍታት በተሀድሶው መስመር እየተሰራ ለውጦች እየመጡም ነው፡፡ አሁን የተከሰተውን ችግርና ፈተና ያለምንም ጥርጥር እንደምንወጣውም እሙን ነው፡፡

በሀገር ሰላም መደፍረስ፣ በንብረት መውደም፣ በዜጎች ሞትና ሕልፈት ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ከሁሉ አሳፋሪው ጎሳና ዘር እየለዩ ጥቃት መፈጸም በእጅጉ ሊወገዝ የሚገባው አሳፋሪና ወራዳ ተግባር ነው፡፡ ሁሉም ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አንተ ትግሬ ነህ፤አንተ አማራ ነህ ፤አንተ ኦሮሞ ነህ፤ አንተ ሶማሌ ነህ እየተባባሉ መናቆርና መባላት መቆም አለበት፡፡ ለሁሉም ኢትዮጵያ ሀገራቸው ናት፡፡ የትም ሄደው የትም ሰርተው በነጻነት መኖር ይችላሉ።

ሁሉም የእኛው ወገኖች፣ የእኛው ወንድሞችና እህቶች ናቸው፡፡ ሕዝብ አይወነጀልም፡፡ ሕዝብ ሰላም ፈላጊ ነው፡፡ ሕዝብ የሀገሩን ሰላምና ደህንነት ከምንም በላይ ይፈልገዋል፡፡ አንድ ሰው ካጠፋ ተጠያቂ መሆን ያለበት በሰራው ሥራ ነው፡፡ በብሔሩ ምክንያት መሆን የለበትም፡፡ ማንም ሰው ከዚህ ብሄር ልወለድ ብሎ በራሱ ፈቃድ የተወለደ በዓለም ላይ የለም፡፡ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ መከበር አለበት፡፡ ፍቅርን፣ መከባበርን፣ መቻቻልን፣ አብሮነትን እንዲሁም ወንድሜ እህቴ መባባልን ከቀድሞውም የበለጠ ማሳደግ አለብን፡፡ ዘረኝነት ሊወገዝና ሊኮነን ይገባዋል፡፡ ለእዚህም ሁሉም ሚዲያ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

የሚያምርብን ሀገርንም የሚያሳድገው አብሮነታችን፣ አንድነታችንና ሰላማችን ነው፡፡ ሀገርን በማተራመስና በሁከት እንድትናጥ በማድረግ የሚገኝ ልማትና ዕድገት የለም፡፡ የተረጋጋ ሰላማችንን ሀገራዊ ልማትና ዕድገታችንን ጠብቀን መራመድ ይገባናል፡፡ ችግሮችን በሰላም፣ በውይይትና በመነጋገር የመፍታት ባሕል ማደግ መጎልበት አለበት፡፡ ትርምሱና ሁከቱ የሚጠቅመው ለሀገር ጠላቶች ብቻ ነው።

ማህበራዊ ሚዲያው ከዚህ የዘረኝነትና የሀገርን ጥፋት ከማራገብ ሕዝብን ከሕዝብ ከማናቆር ሥራው እንዲወጣ መንግሥትና ሕዝብ ተረባርበው መልክ ሊያሲዙት ይገባል፡፡ በዚህ የሰለጠነ ዘመን የጎሳ ፖለቲካን አጀንዳ አድርጎ ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት መስራት አሳፋሪም አሳዛኝ ነው፡፡ ስለዚህም ሊቆም ይገባዋል፡፡

ዛሬ ሀገራችን ኪራይ ሰብሳቢው፣ ሙሰኛው፣ ጥገኛውና የጥበት እንዲሁም የትምክህት ኃይሉ በውጭ ከሚገኘው የፀረ ኢትዮጵያ ኃይል ጋር በመቀናጀት በፈጠረው ትርምስ ውጥረት ውስጥ እንድትገባ ሲደረግ ማህበራዊ ሚዲያው ደግሞ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ የሕዝብን አብሮነት በሚንድ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ በሚያደርግ እርስ በርስ በሚያባላና በሚያናቁር ጥላቻን እንደ ሰደድ እሳት በሚያዛምት እንቅስቃሴ ውስጥ ተነክሯል። በዚህም ሰላም ወዳዱን ሕዝብ ምን ይፈጠር ምንስ ይመጣ ይሆን በሚል ጭንቀት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያው ጠባብነት፣ የዘረኝነት ልክፍትና በሽታ ከልክ በላይ ገዝፏል፡፡ በሰላም፣ በፍቅር፣ በመከባበርና በመቻቻል በክፉና በደጉ ለዘመናት በአብሮነት የኖረውን ሕዝብ፣ ጎሳና ዘር እየለዩ በሀሰትና በውሸት ማስረጃዎች ማባላቱን መደበኛ ሥራ አድርገው ይዘውታል፡፡ ሀገር በእነሱ ታፍራለች፡፡ የቱንም ያህል ችግሮች ቢከሰቱ በቆየውና በነባሩ ባሕላችን በአባገዳዎች፣ በታላላቆች፣ በሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚፈቱና ሊፈቱ የሚችሉ ሆነው ሳለ አላስፈላጊ የሕዝብን ስሜትና መንፈስ የሚያቆስሉ፣ የሚያደፈርሱ እንዲሁም ስሜታዊነትንና ጥፋትን የሚጋብዙ ዘገባዎች፣ ስድቦችና ዘለፋዎች መታየታቸውና መደመጣቸው ሕዝብ እንደመናቅ ይቆጠራልና ሊቆሙ ሊገቱ ይገባቸዋል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያው እየሰራ ያለው አውዳሚ ተግባር ሻእቢያና ግብጽ ከመደቡት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀገርንና ሕዝብን ለማተራመስ ከተበጀተ ዶላር የሥነልቦና ጦርነት ከከፈቱብን የኢትዮጵያን ውድቀት ከሚመኙት ኃይሎች የተለየ አይደለም፡፡ ከሀገር ሰላምና ደህንነት የበለጠ ወሳኝ ነገር መቼም የለም፡፡ሊኖርም አይችልም፡፡ ዋና ዋናዎቹ ሚዲያውም ሆነ ማህበራዊ ሚዲያው በትልቁ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የማረጋጋትና መፍትሔ የማስገኘት ሥራ ነው ሊሰራ የሚገባው፡፡

የተጣራና በማስረጃ የተደገፈ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በመያዝ እንዲታረሙ መንግሥት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጣቸው የማድረግ ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ ማስገኘት ነበር ቀዳሚ ሥራው መሆን ያለበት፡፡ በአንድ ዜጋ ላይ በደል ሲደርስ በራስ እንደደረሰ በመቁጠር ነበር መሰራት የነበረበት፡፡ጎሳና ዘርን በመለየት የሚሰራው ሥራ ከፍተኛ መከፋፈልን፣ ጥላቻና ሀገራዊ ውድቀትን ብቻ ነው የሚያስከትለው፡፡ ለዚህ ነው ሁሉም ሚዲያ ለሰላምና ለሀገራዊ አንድነት መቆም አለበት የምንለው፡፡
 መሐመድ አማን (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment