Tuesday, November 07, 2017

ፌዴራሊዝም የህልውና ጉዳይ

(ጥቅምት 28, (አዲስ ዘመን))--ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ይልቁን የመጨረሻውና ብቸኛው አማራጭ እንጂ። የፌዴራል ሥርዓቱ ለኢትዮጵያ እስትንፋስም ጭምር ነው። ጽንፈኛ አሊያም የትምክህትና ጥበት አካላት የፌዴራል ሥርዓቱን በተመለከተ የሚሰጡትን አስተያየት ልብ ብሎ ላስተዋለ ገራሚ ነው። በጭፍን ጥላቻ ላይ ተመሥርቶ ከድምዳሜ ላይ መድረስ ምን ያህል ስህተት ላይ እንደሚጥል መገንዘብ ምርምርና ጥናት አያስፈልገውም።

ጽንፈኛ አሊያም የትምክህትና ጥበት አካላት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ጠለቅ ብለው ያውቃሉ ብሎ ለማለት አስቸጋሪ ነው፤ ወይም የዚህች አገር ቀጣይ እጣ ፈንታ ግድ አይሰጣቸውም ብሎ ለመግለጽ አያስቸግርም። ለምን ቢሉ የፌዴራል ሥርዓቱን ለማፍረስ መሞከር የኢትዮጵያን እስትንፋስ መዝጋት፣ አገርን መበተን፣ ህዝብን ወደግጭት መክተት እንደሆነ ይሰማኛልና ነው። ይህ የፌዴራል ሥርዓት ለኢትዮጵያ ምን ያስገኘው ውጤት አለ? ለዘመናት በአገሪቱ ይስተዋል የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት እልባት አስገኝቷል? ይህ የፌዴራል ሥርዓት ዛሬ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አስችሏል። ቋንቋቸውንና ባህላቸውን በመጠቀም በማንነታቸው እንዲኮሩ አድርጓል።

ዜጎች አካባቢያቸውን ማልማት በመቻላቸው የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጧል… ሌላም ሌላም። በሁሉም መስኮች የዜጎች መብቶች ያስጠበቀልንን ሥርዓት መነካካት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል በመቻሏ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፖለቲካዊ፣በምጣኔ ሀብታዊና በማህበራዊ ጉዳዮች በተጨባጭነት ተጠቃሚ ሆነዋል።

ለመሆኑ ፌዴራላዊ ሥርዓት ማለት ትርጓሜው እንዴት ይገለጽ ይሆን። ፌዴራላዊ ሥርዓት ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ መንግሥታት (ፌዴራልና ክልል መንግሥታት) በስምምነት የሚፈጥሩት የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን ያጣመረ፣ በቃል ኪዳን ላይ የሚመሠረትና የሚመራ አጋርነት ነው፡፡ አጋርነቱ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን የሥልጣን ክፍፍልና ዝምድናም ይወስናል፡፡የፌዴራል ሥርዓት አንዱ የሌላውን ቅንነትና አብሮ የመኖር እሳቤን በማመን ላይ እንዲሁም አንዱ የሌላውን ልዩ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት በማክበርና በእኩልነት በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ማለት ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን 28 የሚደርሱ አገራት በፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት የሚተዳደሩ ናቸው። 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚተዳደር መሆኑም የፌዴራሊዝም ፀሃፊዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ዴሞክራሲን ለማስፈን ፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች የመንግሥት አወቃቀር መልኮች የበለጠ በመሆኑ 21ኛው ክፍለ ዘመን አገራት ወደ ፌዴራሊዝም አስተዳደር የሚሸጋገሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

አገራት ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥትን ለምን ይመርጣሉ? የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው። ለዚህ አራት ዋና ዋና ምክንያቶች ተጠቃሾች ናቸው። ከነዚህም አንደኛው ምክንያት የፌዴራል ሥርዓት ብዝሃነትን ማስተናገዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ሰፊ ገበያና ትልቅ ኢኮኖሚ የመገንባት ፍላጎት ነው። ሦስተኛው ጠንካራ የመከላከያ ኃይልና የደህንነት ሥርዓት ባለቤት መሆኑ ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ አስተዳደራዊ አመቺነትን መፍጠሩ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓትን እንድትከተል ያስገደዳት ዋናው ነጥብ በአገሪቱ ያለው ብዝሃነት ነው።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት መሠረታዊ ዓላማዎች በህገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ በዚህ መልኩ ሰፍሯል። በአገራችን ባለፉት ሥርዓቶች ይስተዋሉ የነበሩ የተዛባ ግንኙነቶችን ለማስተካከል፣ ቀድሞ ያላቸውን የጋራ አብነቶችና እሴቶች ትስስር ለማጠናከር፣ ዘላቂ ሠላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ለማስፈን፣የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ቃል የገቡ መሆናቸውን፣ ይህን ለማሳካት የግለሰብም ሆነ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች መብቶችና የፆታ እኩልነት ማረጋገጥ፣ ባህሎችና ኃይማኖቶች ያለ አድልኦና ልዩነት እንዲራመዱ ማድረግ ፅኑ እምነታቸው እንደሆነ መወሰናቸው የሚል ነው፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ሁሉን ያሟላ ዘመናዊ የሚባል ህገ መንግሥት ነው። በየዘርፉ ማለትም በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ህዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አንቀጾችንም አካቷል። ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓትን የምትከተል አገር ናት። አገሪቱ በዚህ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረችበት ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግባለች። ፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓቶች የሚለይባቸውን አምስት መሠረታዊ ባህሪያት አሉ። የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት እነዚህን ባህሪያት እንዴት እንደሚጋራ ለማየት እንሞክር።

የመጀመሪያው የመንግሥት አወቃቀርና ተጠያቂነትን ማስፈኑ ነው። ሁሉም የፌዴራል አገሮች ቢያንስ ሁለት መንግሥታት ማለትም ፌዴራልና ክልሎች አሏቸው፡፡ እነዚህ መንግሥታት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። ተጠያቂነታቸውም ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ እነዚህ መንግሥታት ህልውናቸው የሚረጋገጠው በህገ መንግሥት ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር እንደየአገራቱ ሁኔታ ጂኦግራፊያዊ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥት የሚመረጠው በአጠቃላይ የአገሪቱ ህዝብ ነው። የክልል መንግሥት ደግሞ በየክልሉ ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በዋናነት የተዋቀረው በህዝቦች ማንነት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት አደረጃጀት የተመረጠበት ምክንያት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፈው ታሪክ የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን በህገ መንግሥት ዋስትና እንዲያገኙና በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚያስችል አወቃቀር ስለሆነ ነው፡፡

እነዚህ ህዝቦች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሳሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋራ ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው፡፡

የአገሪቱ የአከላለል መሥፈርት ማንነትን፣ ቋንቋን፣ አሰፋፈርንና ፈቃደኝነትን ታሳቢ ያደረገው በህዝቦች የትግል ታሪክ የእኩልነት ጥያቄ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ነው። የማንነት መገለጫ የሆኑትን ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋን፣ ባህልንና ታሪክን ለማጥናት ለመንከባከብና ለማሳደግ ብቸኛ አማራጭ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡

ሁለተኛው የፌዴራላዊ ሥርዓት ባህሪ የሆነው የሥልጣን ክፍፍል ማለትም የራስ እና የጋራ አስተዳደር መመሥረት መቻል ነው። የሥልጣን ክፍፍል የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡

እያንዳንዱ መንግሥት በተሰጠው አስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ ሕግ የማውጣት፣ የመፈፀም፣ የመተርጎምና ገቢን የመሰብሰብ ሥልጣን አለው፡፡ የሥልጣን ክፍፍሉ እንደየአገራቱ ሁኔታ ቢለያይም አገራዊ ጉዳዮችንና አንድነትን ለማስጠበቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሥልጣኖች ለፌዴራሉ መንግሥት የሚሰጡ ሲሆኑ ከክልሎችና ብሄር ብሄረሰቦች ልዩ ሁኔታና ባህል ጋር የተያያዙ ሥልጣኖች ለክልሎች ይሰጣሉ፡፡ በኢትዮጵያም ፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ሕግን የማውጣት፣ ሕግን የመፈፀምና ሕግን የመተርጎም ሥልጣን አላቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በአንቀፅ 51 የክልሎች ደግሞ በአንቀጽ 52 ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ ተለይተው ያልተዘረዘሩ ቀሪ ሥልጣኖች ለክልሎች ተሰጥተዋል፡፡

ሦስተኛው የፌዴራል መንግሥታት ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌዴራል አገሮች የተፃፈ ሕገ መንግሥት ያላቸው መሆኑ ነው። ሕገ መንግሥት የስምምነታቸው ወይም ቃል ኪዳናቸው ማሰሪያ ሰነድ ነው፡፡

በአንድ በኩል አንዱ እርከን ሥልጣኑን ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት የሌላውን እርከን ሥልጣን እንዳይነካ የሚገታው ወይም ሥልጣኔ ተነካ የሚል ካለ ተጠቃሽ ሆኖ የሚያገለግል የተፃፈ ሕገ መንግስት መኖር የግድ ይሆናል፡፡ እንደየአገራቱ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሥርዓት ቢለያይም ሁሉም ፌዴራል አገሮች የሕገ መንግሥታቸውን የተወሰኑ አንቀፆች ያለፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ስምምነት ሊያሻሽሉ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና የኅብረተሰብ ተወካዮች የድርድር ውጤት ነው፡፡

አራተኛው የፌዴራል ሥርዓቶች ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌዴሬሽኖች ሁለት ምክር ቤቶች አሏቸው፡፡ አንዱ "የተወካዮች ምክር ቤት" ወይም "የታችኛው ምክር ቤት" የሚባል ነው። ሌላው ደግሞ "የላይኛው ምክር ቤት’’ ወይም "ሁለተኛ ምክር ቤት" በሚል ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው ምክር ቤት በተለያዩ ፌዴራል አገራት የተለያየ መጠሪያ አለው። በኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ አወቃቀርና ሥልጣኑም እንደየአገራቱ ሁኔታ ይለያያል። የኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ አንድ ውክልና ለተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ተጨማሪ አንድ ወኪል እንዲኖር ያደርጋል፡፡

የምክር ቤቱ ተወካዮች አመራረጥን በተመለከተ በአንዳንድ ፈዴሬሽኖች በቀጥታ በህዝብ ሲመረጡ በሌሎች ደግሞ ከግማሽ በላይ ወይም ከግማሽ በታች ተወካዮች በክልሎች ሥራ አስፈፃሚዎች ይመረጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ አባላቱ በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ ወይም ምክር ቤቶቹ በክልሎቹ ህዝቦች በቀጥታ እንዲመረጡ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበትን መንገድ ይወስናል፣ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ ቀመር በማውጣት ያከፋፍላል፤ ሕገ መንግሥትን ይተረጉማል፣ በክልሎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር መፍትሄ ይሰጣል፡፡

አምስተኛው የፌዴራል ሥርዓት ባህሪያት የሆነው የሕገ መንግስት ጉዳዮች ገላጋይ ተቋም መኖር ነው። የፌዴሬሽኖች ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ክፍፍል ጥቅል፣ መደራረብና መጋራት የሚታይበት ነው፡፡ በመሆኑም በአፈፃፀም ሂደት አንዱ የሌላውን ሥልጣን ሊነካ ስለሚችል በዚህ ጊዜ የሚነሳን አለመግባባት በውይይት መፍታት ካልተቻለ የዳኝነት ፍርድ የሚሰጥ ገላጋይ ተቋም አላቸው፡፡ በዚህ ዙሪያም እንደየአገሩ ልዩነቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ አለመግባባቶችን ግልግል የሚሰጠው ተቋም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መከተል ከጀመረች ጊዜ አንስቶ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነታቸውንና ነጻነታቸውን ማረጋገጥ በመቻላቸው ዘላቂ ሠላም አስፍነዋል። በዚህም ፈጣን ልማት አረጋግጠዋል። ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን ጥቅም ያስገኘላቸውን ሥርዓት መነካካት ወይም ለማፍረስ መሞከር መዘዙ ብዙ ነው።

በመሆኑም በሁለቱም በኩል ማለትም በትምክህትም ሆነ በጥበት የምናስተውላቸውን ጽንፈኛ ኃይሎች መዋጋት የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ይሆናል። ትምክህትና ጥበት የፌዴራል ሥርዓቱ ጠንቆች መሆናቸውን በመገንዘብ የሃሳብ ትግል ልናደርግ ይገባል።
 ወንድይራድ ሀብተየስ (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment