Thursday, November 02, 2017

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለ14 ቀናት ጸሎተ ምህላ እንደምታደርግም አስታውቃለች

(ጥቅምት 23, (አዲስ ዘመን,  (አጀንዳ)))--የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሞኑን በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ለተጎዱ ወገኖች የስድስት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታወቀች። በአገሪቱ የተከሰተው ግጭት ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍንም በቤተክርስቲያኗ የ14 ቀናት ጸሎተ ምህላ ይደረጋል ብላለች፡፡

የቤተክርስቲያኒቷ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አባ ማቲያስ ቀዳማዊ የቤተክርስቲያኒቷ ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ መጠናቀቅን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ላይ እንደገለጹት፤ ዕቅድን በተግባር ለማረጋገጥ፣ ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በአገሪቷ ባሉ ልዩ ልዩ ቦታዎች በተከሰተው ግጭት ለተጎዱ ወገኖች ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ባለው መዋቅር ስድስት ሚሊዮን ብር እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡

የተከሰተው ግጭት ተወግዶ ሙሉ ሰላም እንዲሰፍንም ከጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለ14 ቀናት በመላ አገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶሱ መወሰኑን ፓትርያርኩ አስታውቀዋል።

«አገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር የነፃነት ምልክት እንደሆነች ሁሉ የሰላምና የጸጥታም ምልክት መሆን አለባት» ያሉት ፓትርያርኩ፤ ኅብረተሰቡ በትዕግስት፣ በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመደማመጥና በመግባባት መንፈስ በአንድነት አብሮ እንዲሰራ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪውን ማስተላለፉን ገልጸዋል።

ፓትርያርኩ እንዳመለከቱትም የነገድ፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ለጋራ ልማትና ለኢትዮጵያ ብሎም ለጎረቤት አገሮች ብሩህ ተስፋ የሰነቀውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁንም እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስፈላጊውን ድጋፍ በመለገስ እንዲተባበሩ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡

የአንድ አገር ዕድገትም ሊፈጥን የሚችለው የሃይማኖቱንና የሞራል ስሜቱ የማይወቅሰውን ሥራ ሲሰራ፤ በመልካም ሥነ ምግባር ሲታነጽ፤ የሥራ ክቡርነትን የሚረዳ ትውልድ ሲኖር ነው ብለዋል፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ለ15 ቀናት የተካሄደ ሲሆን፣ በማጠቃለያውም 17 መንፈሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በጸሎት መፈጸሙንም ፓትርያትኩ አስታውቀዋል።
 ጌትነት ምህረቴ (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment