Friday, October 27, 2017

ሠላም ይቅደም

( ጥቅምት 16, (አዲስ ዘመን,  አጀንዳ))--ለአገር ዕድገትና ልማት ወሳኙ የተረጋጋ ሰላም ነው፡፡ በሰላም ውስጥ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሕዝብና አገር ድረስ ያለው ኑሮ፣ ሕይወት፣ ሥራ፣ ትምህርት፣ ንግድ ... ወዘተ ድረስ በእጅጉ የተቆራኘና የተሳሰረ ነው፡፡ ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ሕብረተሰባዊ፣ ብሎም አገራዊ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ብቻ ነው ስለብዙ የነገ ተስፋዎች ሕልሞች መናገር መሥራት የሚቻለው፡፡

ሰላም የሚጠበቀውና የሚረጋገጠው በሕዝብ ንቁ ተሳትፎ ነው፡፡ አገራችን ሰላምዋን ለማስጠበቅ ነቅታ የምትሠራው ሰላም ለሁለም ነገር ከሁሉም በላይ ወሳኝና አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ ሠራተኛው ሠርቶ ለመግባት ተማሪው ተምሮ በሰዓቱ ወደቤቱ ለመመለስ ፋብሪካው ለማምረት ገበሬውም በወቅቱ ለማረስ አዝመራው ሲደርስም ለመሰብሰብ መምህሩም ለማስተማር ነጋዴውም ለመነገድ ነግዶም ለማትረፍ የተጀመሩ አገራዊ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስም ሆነ ተገንብተው ያለቁት እየሠሩ የሚፈለገውን ውጤትና አገራዊ ዕድገት እንዲያስገኙ ለማድረግ የሰፋ አገራዊ ሰላም ያስፈልገናል፡፡

አገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖራት የተሰሩትንም ሆነ በመሠራት ላይ ያሉት አገራዊ የልማትና የዕድገት ፕሮጀክቶች እንዲመክኑ እንዲጠፉ እንዲወድሙ የተጀመሩትም እንዲቆሙ ለማድረግ ረጅም ርቀት ሄደው የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸው ይታወቃል። በሕዝቡም መካከል የዕርስ በዕርስ ግጭት ለመፍጠር የማናከስ የማጋጨት የፈጠራ ወሬና አሉባልታ የሚነዙ በየማሕበራዊ ድረገፁ እጅግ አሳፋሪ የማባላትና የማናከስ ሥራን የሚሠሩ ሕዝብን ብሔረሰብን የሚሰድቡ ዋናው አላማቸው ሲታይ የአገሪቱን ሰላም ማደፍረስ በሕዝቡ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ማድረግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በዚህ ሳይገደቡ የሕዝብ ሀብትና ንብረትን የግለሰቦችንም ጭምር ማውደም አገራዊ ኢኮኖሚውን የማዳከም የንግድ እንቅስቃሴዎችንና ዝውውሮችን የመግታት ሥራዎችን ለማካሄድ ብዙ አይነት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን የሕዝብን ሰላም የሚያደፈርስ ኢኮኖሚውን የሚገታና ሽባ የሚያደርግ የስነ ልቦና ጫናም እንዲፈጠር የሚጋብዝ እንቅስቃሴ የተከላከለውና የገታው ሰላምና መረጋጋቱን የፈጠረው ወደነበረበት ቦታ የመለሰው ሕዝብ ነው፡፡

በተለይ የውስጥ የመልካም አስተዳደርና የሙስና የፍትሕ እጦትና ኪራይ ሰብሳቢውና የጥገኛ ኃይሉ በሕዝቡ ውስጥ የፈጠረውን በደልና መከፋት በመንተራስ የሕዝቡን ጥያቄዎች በመንተራስ አመጽና ሁከት እንዲቀሰቀስ በየቦታው ረብሻ እንዲሰፋ ሥራ እንዲቆም ወዘተ አቅደው የሚሠሩ ክፍሎች የሚረዱትና የሚታገዙት በጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ከዚህ ጀርባ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች እጅ እንዲሁም አገር ውስጥ ባሉ ወኪሎቻቸው አማካኝነት ለጥፋት ሥራ አይሰማሩም ብሎ የሚያስብ ካለ የዋህነት ነው የሚሆነው፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ወሰንተኛ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ያስከተለው ጥፋት በእጀጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ሊሆን ሊደረግ ሊፈጠር የማይገባውም ነበር፡፡

ችግሩን በተለመደው ሰላማዊ የሽምግልና የውይይት የምክክር የድርድር መንገድ መፍታት እየተቻለ ሁኔታው መልኩን እየቀየረ ሄዶ ያልተጠበቀ አደጋን አስከትሏል፡፡ በቀላሉ ሊፈታ ይችል የነበረውን ችግር በማወሳሰብ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲያመራ የግጭቱ መጠን ስፋት አግኝቶ እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ ኃይሎች እንደልባቸው የሚፈነጩበት ነፃ ሜዳ አግኝተው ከርመዋል፡፡
በአንድ አካባቢ የሚፈጠር የሰላም እጦት መደፍረስ ጥፋትና ውድመት በሌላውም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተለያዩ ተጽእኖዎችን ያሳድራል፡፡ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለመረጋጋት ስሜት ይፈጥራል፡፡ የተጽዕኖ አድማሱ በፍጥነት ነው የሚስፋፋው፡፡ በአገር ደረጃ ሲታይ በሕብረተሰቡ ውስጥ የስነልቦና ጫናም ያሳድራል፡፡ ይህንን ችግር በውይይት በመነጋገር ልዩነትን በልዩነት ይዞ የጋራ መግባባት በተፈጠረባቸውና በጋራ በሚያቆሙ ጉዳዮች ላይ አንድ ሁኖ በመቆም የጋራ የሆነውን ሰላም በመጠበቅ ችግሩን መፍታት እልባትን ማስገኘት ይቻል ነበር፡፡

በጊዜ ትኩረት ያለመስጠት ጉዳይ ነው ትልቅ ዋጋ ያስከፈለው፡፡ በሁለቱም በኩል የነበሩት ያሉት የእኛው ወገኖች ናቸው፡፡ የተፈናቀሉት የሞቱትም ሆነ ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ የተደረጉት የእኛው ወገኖች ናቸው፡፡ ሀዘኑም ሆነ ፀፀቱ የጋራ ነው፡፡ በክልል አይለያይም፡፡
በመሰረቱ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር አይጋጭም፡፡ አይጣላም፡፡ ተቻችሎ ተከባብሮ ተዋዶ ተጋብቶ ተዋልዶ የአንዱን ባሕል አንዱ አክብሮ በደስታውም ሆነ በሀዘኑ እኩል ተገኝቶ ተካፍሎ የአንዱን ቋንቋ አንዱ ተናግሮ እንዲህ በአብሮነት ነው ለዘመናት የኖሩት፡፡

ወደፊትም የሚኖሩት፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያባሉት፣ የሚያናክሱት ጥፋትና ውድመት እንዲፈጠር የሚያደርጉት የጥላቻ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ የሚያዛምቱት የሚረጩት ለማናቆር የሚሠሩት የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡ የእነርሱ ተልዕኮ ከውስጥና ከውጭ የፋይናንስ ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው ኃይሎች ጋር የተቀናጀ ነው፡፡ እነዚህን እኩይ አላማን ይዘው ሲንቀሳቀሱ በስውር ሲሠሩ በሕዝቡ ውስጥም ተመሳስለው በመግባት የተገኙ ክፍተቶችን በመጠቀም ሁከት ለማስፋፋት የሚጥሩት ወገኖች አላማቸው አገራዊ ሰላምን ማደፍረስና ቀውስ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡

ይህንን ለአገርና ለሕዝብ አብሮነት አደጋ የሆነ የመሰሪና አክራሪ ኃይሎች ሴራ ማምከን የአገርን ሰላምና አንድነት መጠበቅ የማንም ሳይሆን የሕዝብ ግንባር ቀደም ኃላፊነት ነው፡፡ ተጎጂው የችግሩ ገፈት ቀማሽ በከፋ ሁኔታ ሰለባ የሚሆነው ሰላሙንና ኑሮውን የሚነጠቀው ልጆቹና ቤተሰቡ ችግር ላይ የሚወድቀው ሕዝብ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለሰላሙ አክብሮትና ዋጋ በመስጠት ሲጠብቀው የሚኖረው፡፡
የውጭ ጽንፈኛና አክራሪ ኃይሎች አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጠው የሞቀና የተደላደለ ኑሮ እየኖሩ በአገር ውስጥ እሳት ለመለኮስና ለመጫር የሚያደርጉት ሩጫ ምንም የሚደርስባቸው ወይንም የሚነካቸው ነገር ስለሌለ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት አይነት በአገርና በሕዝብ ችግር የመቀለድና የማፌዝ ያህል ነው፡፡

አገር ቤት የሚፈጠርን ትርምስ እነሱ በሳተላይት ቲቪ እየተከታተሉ በሞቀ ቤታቸው ሁነው በአገር ጥፋትና ውድመት እንዲሳለቁ የሚፈቅድ ሕዝብ የለም፡፡ በጥላቻ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ሕሊናቸው የታወረ ገና ሥልጣን ብናገኝ እናሠራለን እንገድላለን ሰፊ እስር ቤት ሠርተን እናጉራለን ብለው የሚያስቡ ሕሊናቸው በበቀል የነደደና የጨሰ ሰዎች እንዴት አድርገው ለሕዝብና ለአገር ሰላም ያስባሉ ብሎ መጠየቅም ግድ ነው፡፡

እንደነዚህ አይነት አክራሪና ጽንፈኛ ስብስቦች ለአገርና ለሕዝብ ሰላም አይበጁም፡፡ ሊበጁም አይችሉም፡፡ የማሕበራዊ ድረገጽ ልቅና መረን የወጣ ስድቦቻቸው ያላቸውን የደም መፋሰስ ጥማት ገላጭ ሁኖ ያሳያል፡፡ ልዩነትን በልዩነት የማስተናገድ የመቀበል ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖርን ታላቅ ማሕበራዊ እሴትና ፀጋ የናዱ ስለሕዝብ አብሮነት ስለ አገራዊ አንድነት የማያስቡ የማይጨነቁም ናቸው፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የማያከብሩ ከእኛ በሀሳብ የተለየ ጠላት ነው ብለው የሚያስቡ የጨለማ ዘመን አስተሳሰብ የተጠናወታቸው በበቀል ስሜት ተሞልተው የሚጋልቡ ፈረሶችም ናቸው፡፡

የተለያዩ ሀሳቦችን ማዳመጥ መቀበል የተሻለና ለሁሉም የሚበጀውን የተማከለ ሀሳብ መውሰድ በዚህም አገርንና ወገንን ተጠቃሚ ማድረግ ትልቅነት ነው፡፡ ሰላም የሚመጣው ሰላም የሚገኘው ሁሉም ዜጋ ሕዝቡ በአጠቃላይ ለሰላም መከበርና መጠበቅ ፀንቶ መቆም ሲችል ብቻ ነው፡፡ ይህም ይሆን ዘንድ ግድ ነው፡፡ ሰላም ከሌለ አገራዊ ልማት ዕድገት ሠርቶ ማግኘትም ሆነ መለወጥ የለም፡፡ለሁሉም መሰረቱ ሠላምና ሠላም ብቻ ነው፡፡ ሠላም ይቅደም የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
 መሐመድ አማን (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment