Friday, October 27, 2017

የከፍተኛ ባለሥልጣናቱን የመልቀቂያ ጥያቄ እንዲህ አየዋለሁ

( ጥቅምት 16, (አዲስ ዘመን,  አጀንዳ))--ወጣቱ ልጅቷን በጣም ይወዳታል አሉ። የራሷ ቤተሰቦች ግን ሁሌም ያገሏታል። "ኧረ ምኒቷን ጣለብን" እያሉም ያማርሯታል። ምክንያቱም ልጅቷ አይነ ስውር ነበረች። ይህ ወጣት ልጅ ግን ከልቡ ስለሚወዳት ሁሌም ከጎኗ ሳይለይ ከወላጆቿ በላይ ያገለግላታል፣ ይታዘዛታል፣ ያፅናናታል፣ እየመራም ወስዶ ያዝናናታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ቀን ማየት እንደምትችል ተስፋ ይሰጣታል። የትዳር ጓደኛዋ ሆኖ መኖር እንደሚፈልግ ሁሌም ያስረዳታል።

አንድ ቀን በአካባቢው የዓይን የህክምና ባለሙያ ከውጭ እንደመጣና ለተወሰነ ጊዜ ለታማሚዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ልጁ ይሰማል። የሚያፈቅራትን ያችን አይነ ስውር ልጅም ይዟት ከሄደ በኋላ ከሐኪሙ ጋር ተነጋግሮ አንድ ውሳኔ ላይ ይደርሳል። ውሳኔውም ልጅቷ ቀዶ ህክምና እንድታደርግ ነበር። ልጅቷም ቀዶ ህክምናውን አደረገች። ከሁሉ በላይ ሲያጓጓት የነበረው ግን በችግሯ ጊዜ ከጎኗ ሳይርቅ ከወላጆቿ በላይ ሲረዳትና ሲያግዛት የነበረውን ፍቅረኛዋንና የወደፊት የትዳር አጋሯን ማየት ነበር።

ከቀዶ ህክምናውም በኋላ ማየት ቻለች። የመጀመሪያ ጥያቄዋም ፍቅረኛዬን አሳዩኝ የሚል ነበር። ወደ አንድ ጠባብ ክፍል ወሰዱና አንድ ወንበር ላይ ኩርምት ብሎ የተቀመጠ ልጅ አሳይዋት። የልጁ ሁለቱም ዓይኖች በቦታቸው የሉም። ማመን አልቻለችም።

"ይህ አይነ ስውር፤ ጭራሽ ዓይኖቹም ከቦታቸው የለሉ እንዴት ፍቅረኛዬ ሊሆን ይችላል" ብላ ተናገረች። ወላጆቿም መጡና መሰከሩ። ለጋብቻም እንድትዘጋጅ ነገሯት። እርሷ ግን "በፍፁም ባሌ ሊሆን አይችልም" ብላ ጥላቸው ሄደች። የሚገርመው የተሸከመችው ዓይን የልጁ ዓይን እንደሆነ አለማወቋ ነው። (ከድረ ገጽ ላይ ያገኘሁት ታሪክ ነው)።

ይህንን ተረት እዚህ ላይ ማምጣቴ ከወቅቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር ቢመሳሰልብኝ ነው። በተለይም ከኦህዴዱ መስራች አቶ አባዱላ ገመዳና ከኢህዴን/ብአዴኑ መስራች አቶ በረከት ስምኦን የመልቀቂያ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚደመጡ ነገሮች እንደ ተረቱ ሆኖውብኛል። እነዚሀ ሁለት አንጋፋ ታጋዮችና አመራሮች ልጅነታቸውን፣ ዕድሜያቸውን፣ ጊዜያቸውንና ሌሎች ሌሎች የግል የሆኑ ነገሮቻቸውን ሰውተው ዛሬ ላይ የሚታየውን ስርዓት አጎናጽፈውናል። ከነበርንበት የጨለማ ኑሮ ወደ ብርሃን አሸጋግረውናል። ይህ አበርክቷቸው በፍቅር ከተሸነፈውና ዓይኑን አውጥቶ ለወጣቷ አይነስውር ፍቅረኛው ካበረከተው ወጣት ጋር ይመሳሰልብኛል።

አዎን እነዚህ አንጋፋ የዚያ ዘመን ወጣቶች ወጣትነታቸውን ለዚህ አገርና ሕዝብ ሳይሰስቱ በፍቅር አበርክተዋል። ምናልባትም ዕድለኛ ሆነው በሕይወት ተረፉ እንጂ ዛሬ በአካል ላናውቃቸው ታሪካቸውን ብቻ ልንሰማ የምንችላቸው ታጋዮችም ሊሆኑም ይችሉ ነበር። ምክንያቱም እልፎች የማያልፍ የሚመስለውን ቀን ለማሳለፍ አልፈው ቀርተዋልና። ስለሆነም ዛሬ "ከመንግሥት ሥራ አሰናብቱን" ሲሉ በሰለጠነና በተኮተኮቱበት ዴሞክራሲያዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን በሰለጠነ መንገድ መረዳት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ እንደ ወጣቷ አይነስውር ውለታ ቢስ ሆኖ ጥያቄውን ለራስ በሚመች መልኩ መመንዘር ውለታቢስነት ይሆናል።

እኔ በግሌ የሁለቱን አንጋፋ ታጋዮችና መሪዎች የአሰናብቱን ጥያቄ የምመለከትበት የራሴ እይታ አለኝ። እነዚህ አመራሮች በአንድም በሌላም ለእነሱ አሳማኝ ነው ባሉት የራሳቸው ምክንያት በቃን ብለዋል። ይሄንንም ቀደም ብዬ እንዳልኩት በሰለጠነ መንገድ ነው ያቀረቡት። ለዚህ ብቻ ምስጋና እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል እላለሁ። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሌሎች እንዳደረጉት የመሰረቱትን ሥርዓትና አገር ከድተው በሰው አገር ላይ ሆነው አይደለም ይሄንን ጥያቄ ያቀረቡት።

እዚሁ ሆነው እንጂ። ይሄ በዴሞክራሲያዊ አገራት ዘንድ በጣም የተለመደ ተግባር ነው። ለእኛ ግን እንግዳ ስለሆነብን ብቻ አመራሮቹ ያበረከቱትን ሁሉ ወደ ጎን በመተው ሌላ ሌላ ስም እነሰጣቸዋለን። ይሄ ተገቢ አይመስለኝም። ተገቢ ነው የሚል ካለም የወጣቷ አይነስውር ቢጤ መሆኑን ልብ ይሏል።
ምናልባት መከራከሪያው ለምን ለቀቁ ሳይሆን በዚህ ወቅት መልቀቅ ነበረባቸው ወይ ከሆነ የእኔም ጥያቄ ይሆናል።

በግሌ እደግመዋለሁ በግሌ ሁለቱ አመራሮች ካላቸው የበሰለና የጠለቀ የፖለቲካ እውቀት አንጻር ትንሽ ቢቆዩ ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅሙ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለኝም። ወይን የሚጣፍጠው ዕድሜው በጨመረ ቁጥር መሆኑን ሳስብ ደግሞ የእነዚህ ሰዎች በዕድሜም መግፋት እንኳን ነው ከተባለ እድሜያቸው ለመልቀቅ ምክንያት ባይሆን እመርጥ ነበር። ነገር ግን እንዳልኩት ምክንያቱ የእነሱ ውሳኔውም የእነሱ ስለሆነ አከብራለሁ።

እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ግን ሁለቱም ይሄንን አገርና ሕዝብ አስችሏቸው ቁጭ ብለው ይመለከታሉ፤ ሙሉውንና ቀሪውን ጊዜያቸውን በግል ሕይወታቸው ላይ ብቻ ያሳልፋሉ ብዬ እነደማላምን ነው። የ1997ን ግርግር፣ የአምናውን ሁከትና ሌላ ሌላም ፈተናዎችን ያሻገሩ ባለመልካም ተመክሮ የሆኑ መሪዎች ኢህአዴግ ተመሳሳይ ፈተና ቢደቀንበት እጃቸውን አጣጥፈው ይቀመጣሉ ማለት የዋህነት ነው። ስለሆነም ዛሬ ቢለቁም በቁርጥ ቀን አለን እንደሚሉ ስለማውቅ በመልቀቃቸው ብዙም ስጋት አይገባኝም።

በአገራችን ታሪክ ስልጣን የሚለቀቀው በጠብና በጠብመንጃ ሆኖብን እንዲህ ዓይነቱ ሰላማዊ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ብዙ እያስባለን ቢሆንም፤ በሌሎች አገራት ግን የተለመደ ተግባር መሆኑን ልብ ይሏል። ሌላው ሌላውን እንኳን ትተነው የአሜሪካው ዋና ሰው ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን ስንት ባለስልጣኖቻቸው ናቸው በቃኝ እያሉ ስለጣናቸውን የመለሱላቸው። ስለዚህ የስልጣን በቃኝ ጥያቄ በትራምፕ አስተዳደር ሲሆን ትክክል በአቶ ኃይለማርያም አስተዳደር ሲሆን ደግሞ ስህተት ነው ሊባል አይችልም። ስህተት ከሆነ ሁሉም ስህተት ነው፤ ትክክል ከሆነ ደግሞ ሁለቱም ትክክል ነው።
የሁለቱ አመራሮች መልቀቅ የሥርዓት መፍረስ አድርጎ መመልከትም አላዋቂነት ነው።

ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ሥርዓቱ ያበቃለት፤ አገሪቷም የምትፈራርስ አድርጎ በመቁጠር በስደት አገር ላይ ሆነው የሽግግር መንግሥት ሳይቀር ያቋቋሙ ወገኖች እንደነበሩ ልብ ይሏል። ያ ግን ከንቱ ቅዠት እንደነበረ ሲረጋገጥ ወራትም አልፈጀም ነበር። በእርግጥ እነዛ ወገኖች አገሪቷ ከነበረችበት ታሪክና የፖለቲካ ባህል አንጻር ተነስተው እንደዚያ ብለው ቢያስቡና ቢደራጁ ስህተት ላይሆን ይችል ይሆናል። አገሪቷ ግን ዴሞክራሲን መተግበር ጀምራ ነበርና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የመሪዋን ህልፈተ ሞት ተከትሎ ሊመጣ ይችል የነበረውን አደጋ ሳትንገራገጭ እንደ ህልም አልፋዋለች።

አሁንም ዴሞክራሲው እየጎለበተ መሆኑን ዳግም የምንመለከትበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። የአገሪቷ ዋና ሕግ አውጪ በሆነው ተቋም ውስጥ ታላቅ ስልጣን የሆነውን አፈጉባኤነት ተረክበው የነበሩት አቶ አባዱላ አሰናብቱኝ ብለው ጥያቄ አቅርበው አገርም ሥርዓቱም ቀጥሏል። ይሄ የዚህችን አገር ዴሞክራሲ መጎልበት ለሚፈልግና ለአገሪቷ ሰለምና መረጋጋት ለሚመኝ ወገን ሁሉ ትልቅ የምስራች ነው። በአንጻሩ በተቃራኒው ለሚያስብ ደግሞ መርዶ።

እናም እላለሁ የሁለቱን አንጋፋ ታጋዮችና መሪዎች የአሰናብቱን ጥያቄ በአዎንታ ጎኑ ተመልክተን፤ ነገም ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ተገንዝበን፤ ይህ ዓይነቱ አካሄድም ጤናማና በሌሎች አገራትም የተለመደ አሠራር እንደሆነ አምነን እንቀበል። ከዚህ ውጪ የበላንበት ወጪት ባንሰብርና እንዲህ ስለሆነ ነው እንዲያ ስለሆነ ነው በሚል ነገሩን በተዛባ መንገድ ባንመለከተው ምኞቴ ነው። ከዚህ ውጭ ግን እነዚህን ታላላቅ ሰዎች ስልጣን ላይ ቆዩ እያሉ ሲያሙና ሲያሳሙ ኖረው ዛሬ ሰዎቹ በሰለጠነ መንገድ በቃን ሲሉ ሌላ ነገር ማለት "አላዋቂ ሳሚ…" እንደሚያሳኝ ልብ ይሏል።
 አርአያ ጌታቸው (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment