Tuesday, October 31, 2017

የነባር ታጋዮች ሥራ መልቀቅ ሥጋት ወይስ መተካካት?

( ጥቅምት 23, (አዲስ ዘመን))--የኢህአዴግ ሁለት ነባር ታገዮች በቅርቡ የሥራ መልቀቂያ ማቅረባቸውን መንግሥት ይፋ አድርጓል። ነባር ታገዮቹ በራሳቸው ጥያቄ መልቀቂያ ከማቅረባቸው ውጪ ለምን እንደሚለቁ በዝርዝር የተገለፀ ምክንያት የለም። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ወገኖች ጥያቄ ማቅረባቸው ለመተካካት ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ መልቀቃቸውን እንደሥጋት ያነሳሉ። ለመሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችስ ምን አሉ? የመንግሥት ምላሽስ?

የኢዴፓ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው ነባር ታጋዮች ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ሥርዓቱ ግልፅነት ቢኖረው ኖሮ የለቀቁበትን ምክንያት ይገልፅ ነበር። የመገናኛ ብዙሃንም እንዲህ አይነት ነገሮችን መርምሮ በተሟላ ሁኔታ የማቅረብ ነፃነቱ የላቸውም። በመሆኑም ህዝብ የተሟላ መረጃ እንዳያገኝ ሆኗል ሲሉ ይናገራሉ።

የነባር ታጋዮቹ ሥራ መልቀቅ በግልፅ አለመነገሩ ደግሞ ለአገርም ሆነ ለህዝበ ጉዳት እንዳለው ነው የጠቀሱት፤ «እኔም ሆንኩ ሌሎች ብዙ ሰዎች አስተያየት የሚሰጡት በመላምት ነው። የተረጋገጠ መረጃ አግኝተው አይደለም። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ለአሉባልታ በር ይከፍታል። ለሥላምም ጥሩ ያልሆነ ስሜት የሚፈጥር ይሆናል» ይላሉ።

ግለሰቦች የሚለቁት በጤና ምክንያት፣ በብቃት ማነስ፣ በፖለቲካ ልዩነት፣ በሙስና ወይም ደግሞ ተገደው መሆኑ በግልፅ የሚታወቅ አይደለም። ሆኖም በህብረተሰቡ ውስጥ "መንግሥት ተዳክሟል፤ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ክፍተት ተፈጥሯል" የሚል አስተሳሰብ በሰፊው ተፈጥሯል። ይሄ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ይሄ አይደለም ከተባለ መንግሥት የለቀቁበትን ምክንያት በትክክል ለህብረተሰቡ ግልፅ ማድረግ አለበት። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ህብረተሰቡ የተለያዩ መላ ምቶችን ማሰቡ ስህተት እንደማይሆን ይገልፃሉ።

«እኔም በብዛት የማየው መንግሥት እየተናጋ እንደሆነ ነው። ቀደም ሲል በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና በገዢው ፓርቲ መካከል የነበረው ውጥረት ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ደግሞ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ሆኗል። አሁን ደግሞ ውጥረቱ በራሳቸው መዋቅር ውስጥ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አንዳ አንድ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ከተፈጠረው ግጭትና ከባለሥልጣናቱ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ጋር ተያይዞ በራሳቸው ውስጥ መረጋጋት እንደሌለና አለመግባባቶች እንዳሉ ይሰማኛል። ህብረተሰቡም ይህንን እያሰበ ነው። ይሄ መንግሥት እንዲፈርስ ለሚፈልገው የህብረተሰብ ክፍል ደስታን የሚፈጥር ሲሆን መፍረሱን ለማይፈልግ ደግሞ ሥጋት ሊሆን ይችላል። የእኔንም ስሜት በሁለቱ ውስጥ ሆኜነው የማየው። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን መንግሥት ምን ያህል ግልፅነት የሌለው መሆኑን ነው» ሲሉ ይናገራሉ፤ አቶ ልደቱ።

ሌላው አቶ ልደቱ ያነሱት ነጥብ አንድን ህዝብ ለማገልገል በምርጫ የመጣ ግለሰብ ለመመረጥ ለህዝቡ ቃል እንደገባው ሁሉ ሥልጣኑንም ሲለቅ የለቀቀበትን ምክንያት በግልፅ ለህብረተሰቡ መናገር አለበት የሚል ነው። ይሄም አንዱ ኃላፊነትን መወጣት ነው የሚል ዕምነት አላቸው።

« አሁን ባለው ሁኔታ መረጃዎቹ የሚሰሙት በተባራሪ ነው። ስለዚህ ብዥታ መጥራት አለበት። በመንግሥትም ሆነ ኃላፊነታቸውን የለቀቁትና ጥያቄ ያቀረቡት ባለሥልጣናት ዕውነቱን በግልፅ ለህዝቡ መናገር አለባቸው ብዬ አምናለሁ» ይላሉ።
አቶ ልደቱ እንዳሉት ግልፅነት በሌለው መልኩ ሥራን መልቀቅ ግን መተካካት አይደለም። አንድ ሰው በቃኝ ሲል አካሄድ አለ። ግምገማ ይካሄዳል፤ በፓርቲው ደረጃ ጉባኤ ሲካሄድ በጉኤው ሌላ ምትክ ሰው ተመርጦ እነሱም ላበረከቱት አስተዋፅኦ ተመስግነው መሸኘት አለባቸው። ምናልባት የሚወርዱት ተሸልመው መሆን አለበት እንጂ ድንገት ሥራ ለቅቄያለሁ ማለት መተካካት ማለት አይደለም።

ሌላው ይላሉ አቶ ልደቱ፤ ህዝብ ስለመንግሥት ባለሥልጣናት የተሟላ መረጃ የማግኘት መብት አለው። ምክንያቱም የሚፈርዱት በህዝቡ ህይወት ነው። በትክክል ሲሠሩም የሱን ህይወት ነው የሚያስተካክሉት። መጥፎ ነገር ሲሠሩም የህብረተሰቡን ህይወት ነው ችግር ውስጥ የሚከቱት። ስለዚህ ለህብረተሰቡ የማሳወቅ ግልፅ የሆነ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለባቸው። በግራ ፖለቲካ ውስጥ ያለፉ ሰዎች ወይም ድርጅቶች የግልፅነት ችግር አለባቸው። ኢህአዴግም የዚህ ሰላባ ይመስለኛል። ይሄ ለዴሞክራሲው የማይመጥን ውጤቱም ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ነው ባይ ናቸው።

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትግስቱ አወሉ የነባር ታጋዮች ከሥልጣን መልቀቅ ምንም እንዳልሆነ ይናገራሉ። ምክንያቱም አገር የምትመራው በግለሰቦች ሳይሆን በተቋም በመሆኑ የግለሰቦች መልቀቀ ከባድ ጉዳይ አይደለም። የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ከቦታ ቦታ በራሳቸውም ሆነ በሌላ ምክንያት መልቀቅ የውስጥ ጉዳይ ይሆናል። ከዛ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጉዳይ ግን ፖለቲካዊ ይሆናል። ምክንያቱም ተያይዘው የሚመጡ ንግግሮች ምልክቶች አሉት የሚል ግምገማ መኖሩን ይጠቅሳሉ።

አሁን ያለው ሁኔታ መተካካት ሳይሆን የውስጥ ችግር መኖሩን አመላካች ነው። ምክንያቱም መተካካት በህግና በሥርዓት ነው። በውስጥ ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ውስጥ የኃይል አሰላለፍ ይኖራል። የኃይል አሰላለፉ ምናልባት የፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጥሮ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንፃር ካልሆነ በስተቀር መተካካት የሚለው የኢህአዴግ አሠራር ቢሆንም የአሁኑ ግን ከዛ የተለየ ነው። ከታጋዮቹ መልቀቅ ጋር ተያይዞም ግለሰቦቹ የሚሰጡት አስተያየት ይሄንን የሚያረጋግጥ አይደለም።

ህዝቡ መረጃ የማግኘት መብት አለው። ሆኖም ግን ኢህአዴግም ሆነ መንግሥት በባህሪያቸው በቂ መረጃ ሰጥተው አያውቁም። ዛሬ የማህበራዊ ድረገፆች በበዙበት ሰዓት መንግሥት ቀድሞ መረጃ መስጠት ሲገባው በማህበራዊ ድረገፆች የተሳሳቱ መረጃዎችም ይሰራጫሉ። ስለዚህ መንግሥት ቀድሞ የመግለፅ ኃላፊነት አለበት። በተለይ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃንም በዚህ በኩል ወደኋላ ናቸው። በዚህ በኩል ህዝብ በተለይ ስለገዢዎቹ መረጃ የማግኝት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ተነፍጓል። አሁንም ቢሆን መልቀቃቸው ችግር ባይሆንም ለችግሮች ግን ምክንያት ይሆናል። በመሆኑም በውስጥ ሊሠራ የሚገባው በርካታ ሥራ አለ። ኢህአዴግ ይሄንን አላጠናቀቀም የሚል ዕምነት አለኝ ብለዋል።

አቶ ትግስቱ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የሚታየው ብሄረተኝነት የኪራይ ሰብሳቢነት መደበቂያ ነው። በዚህም ፌደራሊዝም ፌደራሊዝምነቱን እንዲያጣ ተደርጓል። ስለዚህ በመንግሥት ወይም በገዢው ፓርቲ በኩል ትልቅ ሥራ ይጠበቃል። ይሄ ሥራ የሚሠራው ከህዝብ ጋር ሆኖ ነው። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ መወሰን ያለባቸው ጉዳዮች መወሰን አለባቸው። እንደ አጠቃላይ ግን ፖለቲካዊ መፍትሄም ያስፈልገዋል። የፖለቲካ መፍትሄም ቢኖርም መጠየቅ የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ካሉ ደግሞ በህግም መጠየቅ ይገባል። ምክንያቱም ይህንን ተከትሎ ሰዎች ሞተዋል፤ ንብረት ወድሟል። የህዝቡ ሠላም መመለስ አለበት፤ አገር እንደአገር መቀጠል አለበት። አሁን ግን ልዩነትን እንደ ጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞ ወደሌላ አቅጣጫ እዳይወስድና የውጪ ኃይል መጠቀሚያ እንዳንሆን ጥንቃቄ መደረግ አለበት ሲሉ ያሳስባሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሐሙስ ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዚህ ጉዳይ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንዳሉት፤ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሥራ ለመልቀቅ በፈቃዳቸው ጥያቄ ማቅረባቸው እንደ አንድ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚገነባ አገር፣ በዴሞክራሲ መርህ ለሚመራ መንግሥትና ፓርቲ ሊገርም የሚገባ አይደለም። በየጊዜውም እንደዚህ አይነት ነገር ሊቀርብ እንደሚችል መለመድ አለበት።

ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች በአገራችን ታሪክ ውስጥ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የነበሩ፤ ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈው በአገራችን ለመጣው ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው። ሳይሰለቹ፣ ሳይታክቱ አቅማቸውንና ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ ያበረከቱ በመሆናቸው አሁን ለምን ወጡ የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሚገርም አይሆንም። ዋናው ጉዳይ ሁለቱ አመራሮች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በተቀራረበ ጊዜ በመሆኑ በአንድነት ያቀረቡና ተመሳሳይ መስለው ሊታዩ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን የተለያዩ ናቸው።

"አቶ በረከት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ይሄ የመጀመሪያቸው ጊዜ አይደለም። ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ጊዜ መሰል ጥያቄ አቅርበዋል። በድርጅቱ ባህል መሰረት በውይይት አሁን ጊዜው አይደለም፤ ወደፊት የሚታይ ይሆናል በሚል መግባባት በትግሉ እንዲቀጥሉ ሲደረግ ቆይቷል። አሁን ግን ጥያቄያቸው ተደጋግሞ የቀረበ በመሆኑና እሳቸውም በዚህ ሰዓት መውጣት እፈልጋለሁ ብለው አቋም በመያዛቸው ምክንያት ድርጅታችን ላደረጉት አስተዋጽኦ ታላቅ ምስጋና በመስጠት ለጥያቄያቸው መልስ እንዲሰጥ ሆኗል" ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ከዚህ በኋላ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ወጥተዋል ማለት ግን ትግል አቁመዋል ማለት እንዳልሆነም ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ የገለፁት። በሚመቻቸው የተለያየ መንገድ ሁሉ ድርጅታቸውን፣ አገርና መንግሥትን ለመደገፍ የሚችሉ በመሆኑ ይሄንን አስተዋፅኦቸውን ሊያበረክቱ እንደሚችሉ በመተማመን ያቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለፃም፤ የአቶ አባዱላ ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ ነው። ጥያቄያቸው ከቀረበ በኋላ ከእሳቸው ጋር ውይይት ተጀምሯል። ነገር ግን ውይይቱ አልተጠናቀቀም። በድርጅቱ ባህል መሰረት ተከታታይ ውይይቶች ይደረጋል። ምንም አይነት ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ እነዚህ ጥያቄዎች ግን በሰከነና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ውይይት ይፈታሉ። ከዚህ አኳያ ውይይቶች ቀጥለዋል። ይሄ ውይይት ውጤቱ ምን እንደሚሆን በሂደት የሚታይ ይሆናል።

"ክቡር አቶ አባዱላ በጎ ፈቃዳቸው ሆኖ ይሄንን ኃላፊነታቸውን እየሠሩ ቢቀጥሉ በእኛ በኩል ደስተኞች ነን። ነገር ግን የእሳቸውንም ፍላጎት እናያለን። በውይይቱ መገባደጃ ላይ እሳቸውም ከመንግሥት የኃላፊነት ቦታ ላይ እነሳለሁ ብለው የሚሉ ከሆነ ፈቃዳቸውን ተከትለን መልቀቂያ ልንሰጥ እንችላለን" ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚነስትሩ የተናገሩት።

ዋናው ጉዳይ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ፣ በትክክለኛው አቅጣጫ የሚመራ መሆኑ ብቻ እንጂ ከዛ ባሻገር መንግሥትም ሆነ ድርጅት ተቋማት ናቸው፤ ብዙ አዳዲስ አመራሮች ይገቡባቸዋል፤ ሌሎች አመራሮችም ይወጡባቸዋል። ስለዚህ በየጊዜው አመራር እየገባና እየወጣ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ አመራሮች እየተተካኩ የሚያሄዱበት ጉዞ ነው። በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመራው ድርጅቱም ሆነ መንግሥት በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሥጋት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ነገር የለባቸውም ሲሉም ጠቁመዋል።

በአንድ የዴሞክራሲ መንገድ በሚመራ ድርጅትና መንግሥት ውስጥ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ አካሄድ ሁሌም ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ ይገባል። እንዲህ አይነት ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በየጊዜው መለመድ አለበት። አዲስ ነገር ተደርጎ መወሰድ የለበትም የአቶ ኃይለማርያም ማጠቃለያ ነው።
 አልማዝ አያሌው (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment