Tuesday, October 24, 2017

ማን ያሸንፋል እንቦጭ ወይንስ ክልሉ? በእኔ እምነት አሸናፊው እንቦጭ ነው!

( ጥቅምት 13, (አዲስ ዘመን,  አጀንዳ))--
ለምን?
ከዚህ ጥያቄ መልስ በፊት ይሄንን ላስቀድም።
‹ሁሉም ሰው ትምህርት ቤት አይገባም፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤት ቢገባም ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቤት አይገባም፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቤት ቢገባም ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት አይማርም፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቢማርም እንኳን ሁሉም እኩል አይረዳውም›።

በእርግጥም እውነት ነው፤ ሁሉም ሰው አንድን ነገር እኩል አይረዳም፤ ቢረዳውም እኩል አይቀበለውም። ቢቀበለውም እኩል አይተገብረውም፤ ቢተገብረውም እኩል ውጤት አያመጣም፤ እኩል ውጤት ቢያመጣም እኩል እኩል … እያሉ መቀጠል ይቻላል። የእኔ ነጥብ እዚህ ላይ አይደለምና ወደ ቁምነገሩ ልለፍ።

አዎን ከአባባሉ መለስ ስል አንባቢ ሆይ እኔም በጣና ላይ ስለተከሰተው አረም (እንቦጭ ይሉታል በዳቦ ስሙ) አደገኝነት ምንም ጥርጥር ባይኖረኝም መፍትሄ ተብሎ እየተተገበረና እየተነገረ ባለው ዘዴ አዋጭነት ላይ ግን ጥያቄ አለኝ፤ ወይንም እንደ አባባሉ እኩል ልረዳ አልቻልኩም።

ወደ ጉዳዬ ከማለፌ በፊት አሁንም ይሄንን ላስቀድም። የአማራ ክልል ኮምንኬሽን ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ እንዲህ የሚል መረጃ አስፍረዋል፤ "ከዛሬ 121 ዓመት በፊት መላው ኢትዮጲያዊያን ወራረውን የጣሊያን ጦር አሳፍሮ ለመመለስ ከየአቅጣጫው በአንድ መንፈስ ወደ አድዋ እንደተመሙት ሁሉ ዛሬም የኦሮሚያ ወጣቶች የሰላሌን ሜዳ ገስግሰው ፤የአባይን በረሀ አቋርጠው በደጀን በኩል ብቅ ሊሉ ነው። ጣናን ሊታደጉ። እኛም "ወትሮም እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን መተሳሰብ፣ መረዳዳት እና መደጋገፍ (በተለይም በክፉ ቀን) ነው እና ስላሰባችሁን፤ ከጎናችን ስለቆማችሁ እናመሠግናለን፤ እንኳን ደህና መጣችሁ (በጋ ነጋን ዱፍተን baga nagaan dhuftan) እንላለን"።

የክልሉ መንግስት በአንድም በሌላም ጣናን እንታደግ ብሎ ያቀረበው ጥሪ እንዲህ ምላሽ ማግኘቱ እጅግ አስደስቶኛል። ከሳምንታት በፊትም በተመሳሳይ በአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት አስተባባሪነት ጣናን እንታደግ በሚል የእግር ኳስ ውድድር ተካሂዶ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የፋሲል ከነማ የስፖርት ከለብ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ጣና ላይ ዘምተው አረሙን ሲነቅሉ ታይተዋል። እንዲያውም በወቅቱ የተነሱ ፎቶዎች እጅግ መነጋገሪያ ሆነው በብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያችን ሳይቀር ተላልፎ ተመልክቻለሁ። ይሄ ይሄ አይነቱ ተግባርም ይመስለኛል ዛሬ የኦሮሚያ ወጣቶችን ወደ ጣና እንዲጓዙ ያነሳሳቸው።

የክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድርና የካቢኔያቸው አባላትም ወደ ሀይቁ ገብተው አረሙን ሲነቅሉ ታይተዋል። ይሄም እጅግ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። መሪ በሁሉም ነገር አርአያ ሲሆን መመልከት አስደሳች ነው። ምክንያቱም ሌላውን ስሩ ለማለት ቅድሚያ ራስ ሰርቶ ማሳየት የሞራል ብቃትን ያጎናጽፋልና ነው።

ምንጊዜም ለክፉ ቀናችን ቀድሞ የሚገኘው መከላከያ ሰራዊታችንም በሃይቁ ላይ ዘምቶ አረሙን በመንቀል ተግባር ላይ ተሳትፏል። በተመሳሳይም የባህርዳር እና የአካባቢው ወጣቶች፣ የጎንደር፣ የጎጃምና የሌሎች አካባቢ ወጣቶች ተመሳሳይ ተግባር አከናውነዋል። ሌላም ሌላም ሌላም። ሌሎችም ሌሎችም።

በቀጣይም ልክ እንደ ኦሮሚያ ወጣቶች ሁሉ ከሌሎች ክልሎች በርካታ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ጣና እንደሚተሙ ምንም ጥርጥር የለኝም። እውነት ለመናገር ህዝቡ በዚህ መልኩ እያደረገ ያለው ርብርብ እጅግ አስደሳች ነው። ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ድረስ በጋራ ጠላት ላይ የሚያነሱት የጋራ ክንድ እንዳለ በመመልከቴም ኩራት ተሰምቶኛል።

ይሄ ሁሉ ርብርብ የሚያስረዳው በእርግጥም ሁሉም ሰው ችግሩን እኩል መረዳቱን ነው። መፍትሄው ላይ ግን ሁሉም ሰው እኩል ግንዛቤ አለው፤ እኩልም ተረድቶታል ለማለት አልደፈርኩም። ምክንያቱም ቢያንስ እኔ በመፍትሄው ላይ ባለመስማማት ይሄንን እየጻፍኩ ነውና። ሌላም ከእኔ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ሰው የሚያቀርበው አመክንዮ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ።

ይሄንን ሁሉ አረሙን የማጥፋት ርብርብ በአጭሩ ስጠቀልለው ክልሉ በእንቦጭ ላይ ዘመቻ ከፍቷል፤ ብዙዎችን ያሰለፈበትን ዘመቻም ለማሸነፍ ከዚህ መጤ አረም ጋር ትንቅንቅ ላይ ነው ማለት እችላለሁ። ጥያቄው ግን፤
ማን ያሸንፋል? ነው።
በእኔ እምነት ክልሉ ለጊዜው ያሸንፋል።
መፍትሄው ላይ ሌላ ሳይንሳዊ አማራጭ ካልተተገበረ ግን ዋናው አሸናፊ እንቦጭ ነው።
ለምን?

ለምንማ፤ እንቦጭ ያለው ተፈጥሯዊ ባህሪ ከክልሉ መንግስት ዘላቂ ያልሆነ መፍትሄ ጋር ተዳምሮ አሸናፊ እንዲሆን ስለሚያደርገው ነው። የእንቦጭን ባህሪ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ያጠኑ ባለሙያዎች የሚሉትን መስማት ተገቢ ነውና ያንን ገለጻ ለመስማት ሞክሬያለሁ።

እንቦጭ በተፈጥሮው ጾታዊም ጾታዊ ባልሆነም መንገድ ነው የሚራባው። (sexually and asexually)። እንቦጭ በቅጠሉም፣ በግንዱም በስሩም መራባት ይችላል። ይህ ተፈጥሯዊ ባህሪው ከፍተኛ የመራባት አቅምን ፈጥሮለታል። አንዲት የእንቦጭ ቅጠል ቁራጭ ወይንም ትንሿ የስሩ ቁራጭ አሊያም ሌላ የእንቦጩ ክፍል የሆነች ትንሽ ቁራጭ ብቻዋን በአንድ ወር ውስጥ 42 ጊዜ ያህል ትበዛለች።

ይህንን የእንቦጭን ተፈጥሯዊ ባህሪ ይዘን እየተካሄደ ያለውን እሱን የማጥፋት ዘመቻ ስንመዝነው የዘመቻውን ዘላቂ መፍትሄ አለመሆን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። በሰው ጉልበት በሚደረገው የእንቦጭ ምንጣሮ ላይ የተቆራረጡ የእንቦጩ ቅጠሎች በሃይቁ ላይ ተንሳፈው ወይንም በእግር ተረግጠው ደለሉ ስር ተቀብረው መቅረታቸው አይቀርም። ይህ ማለት ከእንቦጩ ጸዳ የተባለው የሃይቁ ክፍል በወራት ውስጥ ተመልሶ መወረሩ አይቀርም ማለት ነው።

ይሄ ደግሞ ዝም ብዬ የምለው ወይንም ከእንቦጩ ተፈጥራዊ ባህሪና ሳይንሳዊ ትንታኔው ተነስቼ ያልኩት አይደለም። ይልቁንም በዚሁ ጋዜጣ መስከረም 10 ቀን 2010 ዓም በወጣው ዜና ላይ የክልሉ የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ከሰጡት ማብራሪያ ተመስርቼ ነው። ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተው የእንቦጭ አረም እስከ ሰኔ 2009 መጨረሻ ድረስ በ24 ሺህ ሄክታር ላይ ነበር።

ከዚህ ውስጥ 22 ሺህ አካባቢው ወይንም 93 በመቶው በሰው ሃይል ተመንጥሮ ተወግዷል። የክረምቱን መግባት ተከትሎ ግን አረሙ በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ውስጥ ባሉ አምስት ወረዳዎች ላይ እስከ ሶስት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተመልሷል፡፡ ይሄው አረም ከሀምሌ ወር ጀምሮ ደግሞ ከጣና ሃይቅ ወጥቶ አባይ ወንዝ ላይ እስከ ጭስ አባይ መሄጃ ድረስ ተከስቷል፡፡

ጥያቄው ያለውም እዚህ ላይ ነው። አረሙን ማስወገድ ከተቻለ እንዴት ሊመለስ ቻለ? መልሱ ቀላል ነው። እንቦጭን በሰው ሃይል ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ቅጠሉ ወይንም ስሩ ተቆርጦ ስለሚቀር ተመልሶ በእጥፍ ማገገሙ አይቀርም። እንቦጭ ሲያብብ ደግሞ መስፋፋቱ በብዙ እጥፍ ይጨምራል። እንቦጭ እንደዚህ ነዋ! ስለሆነም አሁንም በሰው ሃይል የሚደረገው ጥረት ጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይደለም። ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለመጠቀም እየሞከሩ ነው። በተቻለ መጠንም ዋናው መፍትሄ ይሄው የቴክኖሎጂ አማራጭ ነውና በፍጥነት መተግበር አለበት።

ቀደም ብዬ በጠቀስኩት ቀን ዜና ላይ ቴክኖሎጂው አለኝ ያሉት ግለሰብ እንቦጭን በማያዳግም መልኩ ከስሩ የማጥፋት አማራጭ ይዘው እንደቀረቡ ነው የገለጹት። ይህንንና ሌሎች በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚፈበረኩ የምርምርና የምህንድስና ውጤቶችን በፍጥነት መጠቀም ይገባል። አሁን እየተደረገ ያለው እሳት ማጥፋት ነው። በዚያ ላይ ሃይቁ ላይ የሚዘምተው ሰው እንቦጩን መንቀሉን እንጂ ተቆርጣ የምትቀር አንዲት ቅጠል ድካሙን ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ መና እንደምታስቀረው መረጃ የለውም። ወይንም ገለጻ አይደረግለትም። ቢደረግለትም በየትኛውም መንገድ የእንቦጩን ስር ሃይቁ ስር ድረስ ጠልቆ ከደለሉ ፈልፍሎ ነቅሎ ያወጣል ማለት አይቻልም፤ ይቻላል ቢባልም ሁሉም ሰው ያንን ያደርጋል ማለት ራስን ማሞኘት ነው።

ስለሆነም እላለሁ የክልሉ መንግስት በእንቦጭ ላይ ዋና አሸናፊ ለመሆን ከፈለገ አማራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በፍጥነት መጠቀም አለበት። ቴክኖሎጂዎችም በአግባቡ መፈተሽ አለባቸው። አንድ አንዱ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያመጣ የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው። ሌላው ደግሞ በሰው ሃይል ከመመንጠር ያልተሻለ አማራጭ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በጀልባ የሚደረግ ምንጣሮ የእንቦጩን ስር ከደለሉ ስር ነቅሎ ስለማያወጣው እንቦጩ መልሶ ማገገሙ አይቀርም። በመሆኑም ሁሉም ቴክኖሎጂ መተግበር የለበትም፤ ሁሉም ቴክኖሎጂ ቢተገበርም ሁሉም መፍትሄ አይሆንም፤ ሀሉም መፍትሄ ቢሆንም ሁሉም አያዋጣምና አዋጩ መንገድ ብቻ ይተግበር።
አርአያ ጌታቸው  (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment