Saturday, October 28, 2017

የምንዛሪ ማስተካከያውና የአገሪቱ የወጪ ንግድ

( ጥቅምት 21, (አዲስ ዘመን,  አጀንዳ))--የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ሰሞኑን የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ እንዲቀንስ ወስኗል። የምንዛሪ ቅነሳ (devaluation) ቋሚና ከፊል ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ባለባቸው አገራት መንግስት ሆን ብሎ የሀገሩ ገንዘብ ከዋና ዋና የውጭ ገንዘቦች ጋር በንጽጽር ያለውን ዋጋ የመቀነስ የሚያሳልፈው ውሣኔ ነው። ኢትዮጵያ ከ1985 ዓ.ም በፊት ቋሚ የውጭ ምንዛሪ ተመን ነበራት። ከዚያ ወዲህ ደግሞ ከፊል ገበያን ተከትሎ የሚለዋወጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአትን የምትከተል ሃገር ሆናለች።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የብር የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ላይ ሶስት ግዜ ማስተካከያ አድርጋለች። ይህም በ1985 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ 2 ብር ከ7 ሳንቲም ሆኖ በቋሚነት የተያዘውን የ 1 ዶላር የብር ምንዛሪ ተመን በ140 በመቶ ያህል በመቀነስ 5 ብር እንዲሆን ተወስኖ ነበር። ከዚህ በኋላ በ2002 ዓ.ም 13 ብር ከ30 ሳንቲም የነበረውን የ1 ዶላር የምንዛሪ ተመን በ16 በመቶ ገደማ በመቀነስ 16 ብር ከ70 ሳንቲም እንዲሆን ተወስኖ እንደነበረ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ 23 ብር ከ40 ሳንቲም የነበረውን የ 1 ዶላር የምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ በመቀነስ 26 ብር ከ90 ሳንቲም እንዲሆን ተደርጓል።

የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ማድረግ ያስፈለገው የብር ዋጋ ከውጭ ሃገራት ገንዘብ ጋር ሲወዳደር መሆን በማይገባው መጠን ውድ በመሆኑ ነው። ይህ ማለት፣ የኢትዮጵያን ምርት ወደውጭ የሚልክ ነጋዴ በውጭ ምንዛሪ - በዶላር የሚያገኘውን ገቢ ወደአገር ቤት አስገብቶ በብር ሲመነዝረው፣ ወደውጭ የላከውን ምርት ሃገር ውስጥ ሸጦት ቢሆን ኖሮ ከሚያገኘው አንሶ ይገኛል ማለት ነው።

ለምሳሌ የዶላር የምንዛሪ ተመን 23 ብር ሆኖ፣ ወደውጭ የሚላክ አንድ ኪሎ ቡና 4 ዶላር ያወጣል ብለን እንውሰድ። ይሄው ቡና በሃገር ውስጥ 100 ብር ይሸጣል ብለን እናስብ። ቡና ላኪ ነጋዴው በዚህ የምንዛሪ ተመን ቡናውን ወደውጭ ቢልከው በብር የሚያገኘው ገንዘብ 92 ብር ብቻ ይሆናል። ይህ በብር የተገኘ ገንዘብ ወደውጭ የላከውን ቡና አገር ውስጥ ሸጦት ቢሆን ኖሮ ከሚያገኘው 100 ብር በ8 ብር ያነሰ ነው። ይህ ሁኔታ ሲኖር የብር ዋጋ ውድ ሆኗል ይባላል።

የብር ዋጋ ውድ በሆነበት ሁኔታ ላኪዎች ምርታቸውን ወደውጭ መላክ አይፈልጉም። ያንኑ ምርት ሃገር ውስጥ መሸጥን ይመርጣሉ። በሌላ በኩል ከውጭ ምርትን ማስገባት አትራፊ ይሆናል። ይህ ሁኔታ የአገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲያሽቆለቁል፤ በሌላ በኩል ወደሃገር ውስጥ ማስገባት እንዲበረታታ በማድረግ የወጪና የገቢ ንግድን ሚዛን ያዛባል። ይሄኔ የውጭ የምንዛሪ ተመንን ማስተካከል የግድ ይሆናል።

አሁን የሚነሳው ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስተካከያ ማድረግ የግድ በሚል ሁኔታ የብር ዋጋ ውድ ሆኗል ወይ? የሚል ነው። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ ይህን የሚያመለክቱ እውነታዎች ታይተዋል። ለምሳሌ ቡና ላኪዎች ለወጪ ንግድ የተዘጋጀውን ቡና አገር ውስጥ ሸጡት ተብሎ በህገወጥነት ሲከሰሱ በተደጋጋሚ ሰምተናል። ይህ ብቻ አይደለም። በለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ የቆዳ ውጤቶችን - ጫማ ለውጭ ገበያ ለመላክ ዓላማ የተቋቋሙ አምራቾች፣ ምርታቸውን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው በተጨባጭ ታይቷል። አምራቾቹ ይህን ማድረግ የሚያስችላቸው ህጋዊ ስምምነት ስለሌላቸው፣ ሆን ብለው ምርታቸውን ከወጪ ንግድ ምርት የጥራት ደረጃ በታች በማድረግ ለሃገር ውስጥ ገበያ ሲያቀርቡ እንደነበረ ይታወቃል።

ይህ ሁኔታ ተባብሶ አብዛኛውን ምርታቸውን ሆን ብለው ከደረጃ በታች ወደማድረግ ሲሸጋገሩ፣ መንግስት ከደረጃ በታች የሆኑት ምርቶች ለአገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ እንዲቃጠሉ የሚል የአሰራር ደንብ ማውጣቱ ይታወቃል። ይህ የሆነው የብር ዋጋ መሆን ከሚገባው በላይ ውድ ስለሆነ ነው። በህጋዊ መንገድ ወደውጭ መውጣት የሚገባቸው ሌሎች ምርቶችም ለምሳሌ ወርቅ በኮንትሮባንድ ከሃገር የሚወጣበት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱም ይህንኑ ያመለክታል።

ይህ ሁኔታ በተለይ ከ2005 ዓ.ም ወዲህ ለታየው የወጪ ንግድ ማሽቆልቆልና የሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ መቀነስ አንዱ ምክንያት መሆኑ ይታመንበታል። በመሆኑም የሃገሪቱን የወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ማድረግ ተገቢ ነው። በተከታታይ ለአምስት ዓመታት እያሽቆለቆለ የሄደውን የወጪ ንግድና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሽቆልቆል ለመከላከል የሚያስችል ብቸኛው እርምጃ እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት።

መንግስትም በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደቆየው፣ የወጪ ንግድ እንዲያሽቆለቁል ያደረጉት ምክንያቶች፤ ኢትዮጵያ የምትልካቸው የግብርና ምርቶቸ ዋጋ በውጭ ገበያ ላይ መቀነስ፣ አገሪቱ ወደውጭ የምትልካቸው ምርቶች በግብርና ላይ የተመሰረቱና ውስን መሆን፣ የግብርና ምርቶች ላይ ምንም እሴት ሳይጨምሩ መላክ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ኪራይ ሰብሳቢነትንም የወጪ ንግዱ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

እነዚህ የወጪ ንግዱ ላይ ተጽእኖ ያሳደሩት ሁኔታዎች ባሉበት ሁኔታ፣ የብር ምንዛሪ ተመን ላይ የሚደረግ ማስተካከያ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም። የምንዛሪ ማስተካከያው የብር ውድ መሆን ያሳደረውን ተጽእኖ ያህል ብቻ ነው የሚያግዘው። እናም የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ለሁሉም ማነቆዎች መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል። ይህ ካልተደረገ የምንዛሪ ቅነሳ ማስተካካያው ብቻ ለውጥ አያመጣም። የምንዛሪ ማስተካከያ ተደርጎ የወጪ ንግዱ መሆን በሚገባው ልክ ወይም ጉልህ በሆነ መጠን የማይሻሻል ከሆነ ጉዳቱ ሊያመዝን የሚችልበት እድል አለ። የጉዳቱ ምንጭ የብር የምንዛሪ ተመን ማስተካከያ በገንዘብ ግሽበት ወይም በዋጋ ንረት ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ነው።

የብር የውጭ ምንዛሪ ላይ የተደረገው የ15 በመቶ ማስተካከያ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው ሸቀጦች ዋጋ በ15 በመቶ እንዲያሻቅብ ያደርጋል። የሃገሪቱ የውጪ ንግድ ሚዛን ወደገቢ ንግድ ስለሚያጋድል የዋጋ ጭማሪው አብዛኞቹ ገበያ ላይ የሚገኙ ምርቶች ላይ የሚያርፍ መሆኑም አይቀሬ ነው። በሃገር ውስጥ የሚመረቱትም የኢንዱስትሪ ምርቶችም ቢሆኑ በከፊል ግብአታቸው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ፣ በሚጠቀሙት ግብአት ልክ ዋጋቸው ማሻቀቡ አይቀርም። በተለይ የሃገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ ሙሉ በሙሉ ከውጭ በሚገባ ነዳጅ የሚሸፈን በመሆኑ ነዳጅ የአገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ በሚጨምረው እሴት ልክ ዋጋው ያሻቅባል። ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ በአገሪቱ ድንገተኛ እመርታዊ የዋጋ ንረት ሊያስከትል ይችላል።

እናም የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳደግ፣ ከወጪ ንግድ የሚገኘውንም ገቢ ለማሻሻል የተወሰደው የምንዛሪ ማስተካከያ እርምጃ፣ የወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ካሳደሩ ምክንያቶች ለአንዱ ብቻ ማለትም ከብር ውድነት ለመነጨው ብቻ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ሁሉንም የወጪ ንግድ ተጽእኖዎች መቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የወጪ ንግዱ በሚፈለገው ልክ የሚያንሰራራው፣ የሃገሪቱን አጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት በማፋጠን የህዝቡን የመግዛት አቅም መደገፍ የሚቻለው። አለበለዚያ የዋጋ ንረት ተጽእኖው ብቻ ነው የሚተርፈን።

ከዚህ በተጨማሪ የምንዛሪ ማስተካከያው የሚያስከትለውን የዋጋ ንረት መቆጣጠር የሚያስችሉ ስርአቶችን መዘርጋት ያስፈልጋል። የምንዛሪ ማስተካከያው የሚያስከትለው የዋጋ ንረት ተጽእኖ የሚያሳድረው ቋሚ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ብቻ በመሆኑ መቋቋም የሚያስችላቸውን መላዎችን የማበጀት ጉዳይም ቢታሰብበት መልካም ነው።

በአጠቃላይ፤ የውጪ ንግዱ እንዲጎለብት ለማድረግ ከምንዛሪ ማስተካከያው ጋር ሌሎችም በወጪ ንግዱ ላይ ተጽእኖ ያሳደሩ ችግሮች መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል። አለበለዚያ የወጪ ንግዱን ላይ የሚገኘው መሻሻል የምንዛሪ ማስተካከያው ከሚያስከትለው የዋጋ ንረት ጫና ጋር አልመጣጠን ብሎ ጉዳቱ ብቻ ይተርፈናል። እርግጥ መንግስት ከምንዛሪ ተመን ማስተካከያ እርምጃ አስቀድሞ ሌሎቹን የወጪ ንግድ ተጽእኖዎችን ስለለየና በአግባቡ ስለተረዳ እርምጃ ለመውሰድም ስለተዘጋጀ የሚፈለገው ውጤት ይገኛል የሚል ተስፋ አለን።
 ኢብሳ ነመራ (አዲስ ዘመን, አጀንዳ)

No comments:

Post a Comment