Tuesday, October 24, 2017

የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ የፋይናንስና የህግ አማራጮች ይኖሩ ይሆን?

( ጥቅምት 13, (አዲስ ዘመን, ዜና ትንታኔ))--ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቷ መገበያያ ብር የመግዛት አቅሙ በ15 በመቶ እንዲቀንስና ባንኮች ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፍሉት ወለድ ሰባት በመቶ እንዲሆን ወስኗል። ይህን ተከትሎም ምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌላቸው የዋጋ ጭማሪዎች እየተስተዋሉ ነው። የምንዛሪ ለውጡ ከዋጋ ግሽበት አንጻር ያለው ተጽዕኖና ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ያሉትን አማራጮች በተመለከተ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ።

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ኃይሌ አደመ እንደሚናገሩት፤ የብር የመግዛት አቅም ከአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ በመቀነሱ የዋጋ ግሽበት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ምክንያቱም በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶች ከፍተኛ በመሆናቸው ነው። ተጽዕኖውን ለመቆጣጠር ደግሞ በዋናነት ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገር ውስጥ የብር ኖቶች ዝውውር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።

እንደ አቶ ኃይሌ ገለጻ፤ ባንኩ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ቁጥጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማጠናከር አለበት። የገንዘብ መጠኑ እንዲቀንስ በማድረግ በአገሪቷ ውስጥ የሚከሰተው የዋጋ ግሽበት እንዳይጨምር ሊቆጣጠር ይገባል። ብሔራዊ ባንክ በገንዘብ ምንዛሪ ዋጋ መውረድ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የንግድ መዛባት ለመቆጣጠር ወደ ገበያ የሚገባው የብር መጠን ከኢኮኖሚው ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ክትትሉን ማስፋት ይኖርበታል። እንደ ኢኮኖሚው ሁኔታ እየታየ እና አላስፈላጊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር በተጠና ሁኔታ ገበያው ውስጥ የሚዘዋወረውን የብር መጠን ማስተካከል ያስፈልጋል።

በርካታ የብር ኖቶች ወደ ገበያ ውስጥ እንዳይገቡ በመቆጣጠር ግሽበቱን ለመቀነስ አስፈላጊ መሆኑን የሚያምኑት መምህሩ፤ ነገር ግን ኢኮኖሚውን በማይጎዳ መልኩ ሥርጭቱን ማከናወን እንደሚገባው ያሳስባሉ። በኢኮኖሚው ውስጥ በቂ የገንዘብ ዝውውር መኖሩ ጠቃሚ በመሆኑ የገንዘብ መጠን ቅነሳው ላይ ከተገቢው በላይ ጫና ማሳደር ደግሞ ሌላ ጉዳት እንደሚያስከትል ይገልፃሉ። ወደ ኢኮኖሚው የሚለቀቀው የገንዘብ መጠን ጥናታዊ ቁጥጥር እና ገደብ ካልተደረገበት ግን የግሽበት መጠኑን በማባባስ ለኑሮ ውድነት መጋነን አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ በበኩላቸው ፤ በአገሪቷ ውስጥ የሚከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለመከላከል ካሉት አማራጮች ውስጥ የንግድ ህግን በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ነጋዴዎች ከብር ምንዛሪ አቅም መቀነስ ጋር ተያይዞ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ የማድረጋቸውን አይቀሬነት በመገንዘብ በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ ምርቶች ላይ ዋጋ ለመጨመር እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ።

የዋጋ ጭማሪ ፍላጎታቸው ደግሞ የሚመነጨው በውድ እቃዎች ላይ የሚደርስባቸውን የሸመታ ዋጋ ለማካካስ በቀላሉ በእጃቸው ላይ ባለው ዕቃ ላይ ዋጋ መጨመር በማሰባቸው የመጣ መሆኑን ያስረዳሉ። በዚህ አጋጣሚ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች ተከስተው ግሽበቱ ሊባባስ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። ግሽበቱ እንዳይባባስ ደግሞ በረጅም ጊዜ ዕቅድ የአገሪቷን የገበያ ሥርዓት ዘመናዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።

እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንዳፈራሁ ማብራሪያ፤ ዋጋ በጨመረ ቁጥር የሚጎዳው ተጠቃሚው በመሆኑ በህግ አግባቡ የተቀመጡ የሸማቾችን መብት የሚያስከብሩ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ እና አላስፈላጊ ጭማሪዎችን ከማስጠንቀቂያ ባለፈ በተግባር መከላከል ይገባል። በተለያዩ የአደጉ አገራት ውስጥ «ሳይኮሎጂካል ዋጋ» እየተባሉ የሚጠሩ የመገበያያ ሥርዓቶች ላይ 15 ነጥብ 99 እንዲሁም 10 ነጥብ 99 እየተባሉ የሚሰጡ የዋጋ ዝርዝሮች ይገኛሉ። በትርፍ ደረጃ የግብር አሰራር ስለተቀመጠላቸው አንድ ሳንቲም እንኳን ቢጨምሩ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የግብር ጭማሪ ደረጃ ላይ የሚደርሰው ዋጋ ውስጥ ምርታቸው ስለሚገባ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ አይደፍሩም።

«የዋጋ ግሽበቱ በአገር ውስጥ ምርቶችም ሆነ ከውጭ በሚገቡት ላይ ሊከሰት ስለሚችል የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር መከላከል ይከብዳል» የሚሉት ደግሞ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሙላይ ወልዱ ናቸው።

የዋጋ ጭማሪው ሊከሰት የሚችለው ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ በሚመረቱት ላይ መሆኑ ምክንያታዊ መሆኑን ይጠቁማሉ። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም አገር ውስጥ የሚመረቱ አብዛኛዎቹ ምርቶች ግብዓታቸው ከውጭ አገራት የሚገቡ በመሆኑ ዞሮ ዞሮ ግብዓቱ እና ማምረቻ መሳሪያው የሚመጣው በውጭ ምንዛሪ እንደሆነ ያስረዳሉ። የዋጋ ግሽበቱ ምክንያታዊ ቢሆንም ከመጠነኛው የዋጋ ጭማሪ በላይ ዋጋ የሚያቀርቡ አካላት ሲቀርቡ ብቻ አስተዳደራዊ መፍትሄ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት ላይ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የብር ምንዛሪ አቅም እንዲቀንስ ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀደም ባሉት ጊዜያት የምንዛሪ ማሻሻያ በተወሰደበት ወቅት በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መከሰቱን በመጠቆም በአንድ ጊዜ ከፍተኛ የምንዛሪ ለውጥ ማድረግ ሊያመጣው ከሚችለው ጥቅም በላይ ጉዳቱ ሊከፋ እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል።

እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሙላይ እምነት፤ በአሁኑ ወቅት ግን የዋጋ ግሽበት ሊያባብስ የሚችል ክስተት እየተስተዋለ ባለመሆኑ የገበያው ሂደት እና የዋጋ ግሽበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሎ መናገር አይቻልም። በመሆኑም ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስፈልግበት ጊዜ አይደለም።

በአንድ በኩል የዋጋ ግሽበት ሊከሰት ስለሚችል የአገሪቷን የገንዘብ ዝውውር የተጠና ገደብ ሊበጅለት ይገባል። በተመሳሳይ ችግሩን ለመቆጣጠር የህግ እና የግብር አሰራሮች የዋጋ ጭማሪን የማያበረታቱ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል የዋጋ ጭማሪ በአገሪቷ መከሰቱ አይቀሬ ቢሆንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ባለመሆኑ በፍጥነት እርምጃዎች ላይ መሳተፍ አያስፈልግም የሚል መከራከሪያ ሃሳብ አቅርበዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንዳፈራሁ በበኩላቸው፤ ነጋዴዎቹም በነጥቦች ደረጃ ዋጋቸውን የሚያስቀምጡት የትርፍ መጠናቸው ላለማለፍና ከግብር ዕዳ ለመዳን በማሰብ ነው። በኢትዮጵያም ነጋዴ እስከ አዋጣው ድረስ ይሽጥ ብሎ መልቀቅ ተገቢ አይሆንም። ነጋዴዎች ዋጋ በጨመሩ ቁጥር የሚጣልባቸው የግብር ሁኔታ እያደገ ቢሄድ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚደፋፈር ሻጭ እንደማይኖር እና የኑሮ ውድነቱንም ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ያስረዳሉ።
ጌትነት ተስፋማርያም (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment