Wednesday, September 20, 2017

''..የሞተው ወንድምሽ የገደለው ባልሽ - የሰሞኑ ግጭት''

(መስከረም 10, (አዲስ ዘመን))--የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች አንዳንድ ጊዜ ከአገር ውስጥ ተወሳኞች እንዲሁም ከውጭ አገራት ድንበረተኞች አርብቶ አደሮች ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል። ግጭቱ አንድም ከእንስሳት መኖ አሊያም ከውሃ ፍላጎት ጋር ይያያዛል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ አዋሳኝ ቀበሌዎችም የግጦሽ መሬት እና ውሃን ለመጠቀም በሚደረግ ጥረት የተለያዩ ግጭቶች መከሰታቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ችግሮቹ በተከሰቱባቸው የወሰን አካባቢዎች የሚገኙ የሁለቱም ክልሎች የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ግጭቱን በእርቅ እና በካሳ አስማምተው ሲያበርዱትና ሲያደርቁት ኖረዋል።

ሰሞኑን በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰተው ግጭት ግን ከዚህ ለየት ያለ ነው። አስተዳደራዊ ወሰን ይገባኛልን ምክንያት አድርጎ የተነሳው ግጭት በአዋሳኝ ቀበሌዎች ላይ ሳይወሰን በከተሞችም የንጹሃን ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፤ እንዲፈናቀሉም አድርጓል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እንደሚናገሩት ፤ ግጭቱ የብዙዎችን ልብ ሰብሯል። በዚህም የኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ መላውን የአገሪቷን ህዝብ ጥልቅ ኀዘን ውስጥ ከቷል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በሚኖሩ ህዝቦች መካከል መጠነኛ ግጭቶች ቢያጋጥሙም፣ አሁን የተከሰተው ግን የከፋ ጉዳት ያስከተለ ሆኗል።

ህዝቦቹ በመፈቃቀር እና በአንድነት ተባብረው የሚኖሩ ናቸው። ይህን መፈቃቀር እና ሰላም የማይፈልጉ ሰዎች እያካሄዱት ያለው ድርጊት ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ጉዳት በማሰብ ከወዲሁ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

«በሶማሌ ወንድሞቻችን እና በኦሮሞ ቤተሰባችን ላይ የደረሰውን የህይወት መጥፋት እና ከቀዬ መፈናቀል እናወግዘዋለን» ያሉት አቶ ለማ፤ የተፈጸመው እኩይ ድርጊት እንደ ቀላል ሊታይ የሚገባው እንዳልሆነ እና ነገም እንዳይደገም ከወዲሁ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።

ከወሰን ጉዳይ የዘለለ እና አዝማሚያው አደገኛ መሆኑን በመግለጽም ከወዲሁ ሊቀጭ እንደሚገባው ይናገራሉ። ‹‹ ይህ እኩይ ድርጊት በተወሰኑ ወንጀለኛ ግለሰቦች አነሳሽነት የተፈጸመ እንጂ የሁለቱንም ክልል ህዝብና መንግሥት የሚወክል ተግባር አይደለም›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ህዝቦቹ ለዘመናት ተዋልደው እና ተግባብተው በመኖራቸው ወንድማማችነታቸው ጎልቶ የሚታይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ አዝማሚያው ከባድ የሆነውን ይህን ችግር ህብረተሰቡ እና መንግሥት ተባብረው ሊመክቱት ይገባል። በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን በአፋጣኝ ለማስቆምና የተፈናቀሉትን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም በጋራ ለመስራት ክልሉ ቁርጠኛ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት፣ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በግጭቱ ምክንያት ምንም ዓይነት መረበሽ እና 'እኛም ከክልሉ እንወጣ ይሆን' የሚል ስጋት ሳያድርባቸው በተረጋጋ ሁኔታ ህይወታቸውን ሊቀጥሉ ይገባል።

መላው ህዝብም ግጭቱን ለማስቆም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በግጭቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን ለህግ በማቅረብ ሂደት ተባባሪ መሆን ይጠበቅበታል ። የክልሉ መንግሥትም የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ በመሆንም አስፈላጊውን የፀጥታ ኃይል መድቧል። በቀጣይም በግጭቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠትም ሆነ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ከፌዴራል መንግሥትና ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አስተዳደርና ህዝብ ጋር በጋራ ይሰራል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ እንደሚገልጹት፤ ክልሎቹ በሚዋሰኗቸው ረጅም የድንበር አካባቢዎች አነስተኛ ግጭቶች ማጋጠማቸው ተለምዷል ፡ግጭቶቹም ችግሩ በተፈጠረበት የድንበር አካባቢ ብቻ የሚያበቁ ናቸው። ሌሎች ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ለጉዳት የሚዳርጉ አይደሉም፡፡

አሁን እየታየ ያለው ከዚህ የተለየ መሆኑን አቶ አብዲም ይገልጻሉ፡፡ የወሰን ችግር በሌለባቸው ከተሞች ጭምር ግጭቱ ተስፋፍቶ የንጹሃንን ህይወት መቀጠፉንና በርካታ ሰዎችን ማፈናቀሉን ጠቅሰው፣ ድርጊቱ ሊወገዝ እና አፋጣኝ እልባት ሊያገኝ እንደሚገባው ያስገነዝባሉ።

ግጭቱን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አብዲ፤ የኦሮሚያ እና የኢትዮጰያ ሶማሌ ክልል አመራሮች በጉዳዩ ላይ በጋራ የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚተባበሩ ይናገራሉ። ሰላም እና መረጋጋቱን መልሶ ለማምጣትም ቀን ከሌት እንደሚሰራም ያረጋግጣሉ። ህዝቦቹ በአንድነታቸው እንዲቆዩ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል ይላሉ።

በኦሮሚያም ሆነ በኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ላይ የተፈጸመው ድርጊት የሚወገዝ እና ህዝብንም ሆነ መንግሥትን አይወክልም። ከሁለቱ ህዝቦች ባህል እና የአብሮነት ታሪክ ያፈነገጠ የጥፋት ተግባር መሆኑንም ህብረተሰቡ ሊረዳ ይገባል። በድንበር አካባቢ የሚታዩ ግጭቶችን ለመቀነስ በቀጣይ የትጥቅ ማስፈታት እና ወደ ህገ መቅረብ ያለባቸውን ግለሰቦች ለፍትህ ማቅረብ ይገባል። ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ከሚያደርገው ሥራ በተጨማሪ ክልሉ አስፈላጊውን የሰላም ማስፈን ሥራ ያከናውናል።

ርካሽ ፖለቲካን መሰረት ያደረገ የጥፋት ዘመቻ የሚከተሉ ግለሰቦችም ከድርጊታቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል።የጥፋት ኃይሎች በመገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩትን የሃሰት ዘገባ ማቆም ይገባቸዋል። የንጹሃን ደም በከንቱ ፈሷል፡፡የተፈናቀሉ ዜጎች ችግር ላይ እየወደቁ ናቸው፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር አካባቢዎች ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ «በአሁኑ ወቅት በቅድሚያ በክልሎቹ የተለያዩ ቦታዎች የሚካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችን ማስቆም ያስፈልጋል»ይላሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በግጭቱ ምክንያት የተጣሉትን ዜጎች ማስታረቅ እና የተጎዱትን መካስ ይገባል። ለዚህም በዋነኛነት የክልሉ አመራሮች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።የተፈናቀሉትን ወደ እየቀዬቸው በመመለስ ወደ ተረጋጋ ህይወት እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው። የፌዴራል መንግሥቱም ተፈናቃዮችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የማስተባበሩን ሥራ ማከናወን ይኖርበታል።

በዚህ የጥፋት ድርጊት እጃቸው ያለበት አካላት ተለይተው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ድርጊቱ የተሳሳተ ዓላማ የሚያራምዱ አካላት የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት አደጋ ላይ ለመጣል አስበው የፈጸሙት መጥፎ ተግባር በመሆኑ በአፋጣኝ መፍትሄ ማግኘት ይኖርበታል። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙም ሆነ ከመዋቅሩ ውጪ የሆኑ ግለሰቦች በግጭቱ ውስጥ እጃቸው ካለበት የሰው ህይወት ቀጥፎ በሰላም መኖር ስለማይቻል አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።

የክልሎቹ አዋሳኝ ቀበሌዎችን የድንበር ማካለል በተመለከተ እስከ 2006 አጋማሽ ድረስ በተከናወኑ ህዝበ ውሳኔዎች መሰረት 274ቱን ማካለል መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ ። ከ2006ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በፋፈን፣ በነጎብና በሲቲ ዞኖች ስር በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች የወሰን ማካለል ሥራ ለማካሄድ የተደረገው ጥረት በመዘግየቱ ለበርካታ ወገኖች ጉዳት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ተብሎ ሲተች ነበር።

በቀሪዎቹ ቀበሌዎች የማካለሉን ሥራ ለማከናወን እና በሁለቱ ክልሎች አጎራባች በሆኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚኖሩ ህዝቦች ሲከሰቱ የነበሩትን ግጭቶች በዘላቂነት ለመፍታት ባለፈው ሚያዚያ ወር 2009 ዓ.ም በክልሎቹ መካከል ስምምነት መደረሱ ይታወሳል። በሰባት ዞኖች 33 ወረዳዎች ስር የሚገኙ 148 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል የአስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ስምምነት ሲፈረምም ለተፈፃሚነቱ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ኃላፊነት ወስደዋል።

ባለፈው ነሐሴ 2009 ዓ.ም በክልሎቹ የ85 አጎራባች ቀበሌዎችን ወሰን የማካለል ሥራ ማከናወን መቻሉን ከክልሎቹ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ይሁንና ቀሪ 63 ቀበሌዎችን የማካለሉ ሥራም እየተካሄደ ነበር። በስምምነቱ መሰረት ከዚህ ቀደም ሳይካለሉ የቀሩትን ጨምሮ በምዕራብ እና ምስራቅ ሀረርጌ፣ ባሌ፣ ጉጂ እና ቦረና ዞኖች እና ቀበሌዎች የማካለል ሥራ እየተከናወነ ነበር።

በወሰን ምክንያት ደፍርሶ የነበረው የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ወደ ቀድሞው እየተመለሰ ባለበት ወቅት ነው ይህ የሰሞኑ ድንገተኛ ግጭት ተነስቶ የዜጎችን ህይወት የቀጠፈው።

ጌትነት ተስፋማርያም (አዲስ ዘመን)

No comments:

Post a Comment