Friday, July 10, 2015

ኦባማ ኢትዮጵያን ለምን ይጎበኛሉ? (ከ እያዩ ዓለማየሁ)

(ሐምሌ ፫ /2007, (አዲስ አበባ))--"የኦባማ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ዕቅድ አገሪቱ ለአሜሪካ ያላትን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የሚያረጋግጥ ነው" - ፒተር ፓም በዚህ በያዝነው የሐምሌ ወር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት እንደሚመጡ የአሜሪካ መንግስት ይፋ አድርጓል።

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት ከመንግስት ባለስልጣናትና ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን መሪዎች ጋር ይወያያሉ። ኦባማ በቆይታቸው በኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብታዊ እድገት ግስጋሴ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር በሚችሉበትና በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩም ነው የሚጠበቀው።

ፕሬዚዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በኬንያ ዓለም አቀፍ የንግድ ኢንተርፕርነርሽፕ ጉባዔ ላይ እንደሚካፈሉ ይጠበቃል። ጋና ፣ ግብፅ ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ በፕሬዝዳንት ኦባማ የተጎበኙ የአፍሪካ አገሮች ናቸው።

የኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሰረተ 112 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ባራክ ኦባማ በስልጣን እያሉ ኢትዮጵያን የጎበኙ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ያደርጋቸዋል። ይህንን አስመልክቶ የአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ዳይሬክተር ፒተር ፓም የፕሬዚዳንቱን የጉብኝት ዕቅድ አሜሪካ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ጠቃሚነት ስለመረዳቷ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን በምክንያት ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነት ከመሰረተች ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ተቆጥሯል የሚሉት ፓም ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደገ ከሚገኙ አምስት የዓለም አገራት መካከል አንዷና ለበርካታ ዓመታት ባለሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለች አገር መሆኗን ያነሳሉ።

አገሪቱ እያስመዘገበች የምትገኘው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከዓለም አገራት ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት በእጅጉ እያሳደገላት ይገኛል። በንጽጽር ሲታይም ኢትዮጵያ እንደ ጨርቃጨርቅ እና ቆዳ ላሉ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት ዋነኛ መሠረት የሆኑትን ግብዓቶች፣ ሰራተኛና የኤሌክትሪክ ኃይልን በአነስተኛ ዋጋ በማቅረብ በኩል አንጻራዊ ብልጫ አላት።

ይህንን በመመልከትም በርካታ ባለሃብቶች የሰው ጉልበትና ግብዓትን የመሰሉ የኢንዱስትሪ መሰረቶች ዋጋ እየናረ ከሚገኝባቸው አገራት ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ምስራቅ አፍሪካዊት አገር እየተመሙ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢኮኖሚያዊ ዕድገቷም ሆነ በምትከተለው ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም አሜሪካን እየፈተነቻት የምትገኘው ቻይና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት መስክ በስፋት እየተሰማራች ትገኛለች።

"ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝብን በመያዝ ከአህጉሪቱ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ይህች አገር ለአሜሪካ ኩባንያዎች የተመቸች እንደመሆኗም የኦባማ ጉብኝት አንዱ አላማም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት የኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚያዊ  ግንኙነት ማሳደግና ኩባንያዎቿን ተጠቃሚ ማደረግ ነው" ሲሉ የጉብኝቱ አንዱ ዓላማ ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፒተር ፓም ገለጻ ለመረዳት እንደሚቻለው አሜሪካ ኩባንያዎቿን በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ መፈለጓ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን ለማስፋት ብቻ ያለመ ሳይሆን በአገሪቱ የኢንቨስትመንት መስክ በስፋት እየተሰማራችና ምርቶቿን በርካሽ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ የአሜሪካን ኩባንያዎች እየፈተነች  የምትገኘውን ቻይናን በቅርበት ለመፎካከርና የበላይነቷን ለማሳየት መፈለጓንም የሚያሳይ ነው።

ፒተር ፓም ለፕሬዝዳንት ኦባማ ጉብኝት ሌላ መነሻ አድርገው የሚያነሱት ጉዳይ የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነትና ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን የፖለቲካ ማዕከልነት ነው።

ፓም እንደሚሉት ኢትዮጵያ 54 አባል አገራት ያሉት የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ የአህጉሪቱ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ማዕከል ስለሚያደርጋት ለአሜሪካ ያላትን ጠቀሜታ የሚያጎላው ጉዳይ ነው።

የደርግ መንግስት ይከተል በነበረው የማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ከሶቭየት ህብረት ጋር አብሮ አሜሪካን ወደ ጎን ከማድረጉ በስተቀር ኢትዮጵያ ታሪካዊ የአሜሪካ አጋር መሆኗንም ፓም ያትታሉ።    "ሰላምና መረጋጋት በራቀው የአፍሪካ ቀንድ ሰላሟን ያረጋገጠችና የሌሎችንም ሰላም ለማስጠበቅ የምትታትር በመሆኗ ለፔንታገን ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት አገር ናት ” ሲሉም ነው ፓም ሁለተኛ ምክንያታቸውን የሚያስቀምጡት።

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ሁነኛዋ የዋሽንግተን አጋር ሆና እየሰራች መሆኗንም ተንታኙ ያስረዳሉ። ፒተር ፓም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰላም በማስከበር ረገድ እየተጫወተ ያለውን ወሳኝ ሚና የኦባማ የጉብኝት ዕቅድ ኢትዮጵያ ለዋሽንግተን እጅግ ጠቃሚ ስለመሆኗ ሌላው ማሳያ አድርገው ያነሱታል።

ፓም እንደሚሉት ሰራዊቱ በሶማሊያ የአልሸባብን የሽብር እንቅስቃሴ በማዳከም እንዲሁም በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የበምትገኘው የአቢዬ ግዛት የኢትዮጵያ የፖሊስ ሰራዊት አባላት የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ የሰላም ጦርን በዋናነት እየመሩት ይገኛሉ።

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሰራዊት በማዋጣት ረገድ ከአፍሪካ በመጀመሪያ ከዓለም ደግሞ በአራተኛ ደረጃ እንደምትገኝ የሚጠቅሱት ፓም ይህም ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይና እንደ አሜሪካ ባሉ ኃያላን አገራት ከፍተኛ ተቀባይነትን ያስገኘላት ተግባር መሆኑን ነው የሚያስረዱት። 

"ከደርግ መንግስት ውደቀት በኋላ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ መረጋጋት የአስተዳደር መሻሻል አምጥቷል፤ በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉ ኢትዮጵያ በአንድ ትውልድ ዕድሜ ውስጥ ተዓምር ሊባል በሚችል ሁኔታ ከነበረችነት የድህነት አዘቅት ውስጥ በፍጥነት ማንሰራራት ችላለች” የሚሉት ፓም "አገሪቱን ከአንድ ጊዜ በላይ የጎበኘ ሰው አገሪቱ የምታሳየው ለውጥ ቀጣይነት ያለው መሆኑን በቀላሉ ይገነዘባል” ሲሉም ተናግረዋል። "የሁለቱ አገራት መንግስታት የፕሬዝዳንቱን የጉብኝት ዕቅድ የሚቃወሙ ሰዎች አይጠፉም፤ ነገር ግን የኦባማ ጉብኝት አገራቱ ያላቸውን ወዳጅነት ለማጠንከርና የሚለያዩበትን ጉዳይ ማጥበብ ነው ይላሉ።

ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንጻር የዋሽንግተንን ፍላጎት ለማስፋት ያለመ ነው" ሲሉም ነው ፒተር ፓም የኦባማን የኢትዮጵያ ጉብኝት ዓላማ ያብራሩት። የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግስትም አገሪቱ ትርጉም ያለውና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ዕድገት ማስመዘገቧ፤ ሰላም በራቀው አካባቢ ሰላሟን ማረጋገጥ መቻሏና ተሰሚነቷ እያደገ መምጣቱ በዓለም አገራት መሪዎች የጉብኝት ራዳር ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል ብሏል።

የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን “ባራክ ኦባማም ሆኑ የሌሎች አገራት መሪዎች ኢትዮጵያን የሚጎበኙት አገሪቱ ባስመዘገበችው ስኬትና ከራሷ አልፋ የሌሎችን ሰላም ማስጠበቅ በመቻሏ ነው” ብለዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
 Home

No comments:

Post a Comment