Tuesday, July 07, 2015

ቤተክርስትያኗ በአይ ኤስ ለተገደሉ ወገኖች ቤተሰቦች 400 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገች

(ሰኔ 25/2007, (አዲስ አበባ))--በስዊዘርላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን በአይ ኤስ ለተገደሉ ወገኖች ቤተሰቦች ከ400 ሺህ ብር በላይ ስጦታ አበረከቱ።

ድጋፉ የተደረገው ለ11 ተጎጂ ቤተሰቦች ሲሆን ለእያንዳንዳቸው 27 ሺህ 500 ብር በአጠቃላይ ከ 400 ሺህ ብር በላይ ተብርክቶላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ግለሰቦች እጅግ ችግረኛና በእድሜ የገፉ ስድስት ቤተሰቦችን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።

የቤተክርስትያኗ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት "ቤተክርስትያኗ ይሄን አሰቃቂ ድርጊት ከሰማችበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት አከናውናለች"። ሰምዓታቱን ለሰባት ቀናት በተለያዩ የጸሎት ስነስርዓት ያሰበች ሲሆን በቤተክርስትያን የሰማዕትነት ክብር እንዲያገኙም ተደርጓል ብለዋል።

''የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ምንም ዋስትና ወደ ሌለበት አገራት እንዳይሰዳዱ ትልቅ ትምህርት ነው'' ያሉት ጳጳሱ በቀጣይም ቤተክርስትያኗ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ትሰራለች" ብለዋል።

ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወከሉት አምባሳደር ሙሌ ታረቀኝ በበኩላቸው መንግስት ችግሩን ከምንጩ ለመድረቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል። ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተከብሮ በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ለማስቻል የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ከማስፋፋት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ዜጎች ከአገር ሲወጡም ሆነ በሄዱበት አገር መብታቸው ተከብሮ ሰርተው ራሳቸውንና አገራቸውን መጥቀም እንዲችሉ ሂደቱ ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። ችግሩ እየተባባሰ የሚገኘው በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በመሆኑ ወንጀለኞቹን መቅጣትና ማስተማር የሚስያችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑንም ነው ያሳወቁት።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የቤተሰብና የኃይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ በመሆኑ በተለይ የኃይማኖት አባቶች ዜጎች የዚህ አደጋ ሰለባ እንዳይሆኑ የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። ከአገር ውጪ የሚገኙ ዜጎችም አገር ቤት ላሉ ወገኖቻቸው ስላሉበት ሁኔታና ስለ አገራቱ ተጨባጭ መረጃ በመስጠት ጥረቱን ሊደግፉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

1 comment:

Anonymous said...

May God bless you ALL. This is a very good thing we Ethiopians got to support each other and Thank you all the Church members, the Government and everyone who are trying to solve this kind of situations. Thank you Aba and thank you also our Government for taking care of your citizens. God bless Ethiopia and the whole World Amen

Post a Comment