Monday, June 01, 2015

ቤት እያላቸው ኮንዶሚኒየም የሚወስዱትን ተጠያቂ የሚያደርግ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው

(ህዳር 24/2007, (አዲስ አበባ))--ቤት እያላቸው በህገ ወጥ መንገድ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) የሚወሰዱትን፣ እየቆጠቡ ያሉና ወደ ፊት ለመውሰድ የሚሞክሩትን ተጠያቂ የሚያደርግ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ቤት ያላቸው ግለሰቦች ኮንዶሚኒየም መውሰድ እንደማይችሉ መመሪያው ቢያስቀምጥም፤ ተጠያቂ የሚደረግበት አሰራርና ህግ ባለመኖሩ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል። አሁን ግን በህገ ወጥ መንገድ ቤት የወሰዱ፣ እየቆጠቡ ያሉና ወደ ፊትም ለመውሰድ የሚሞክሩ አካላትን የሚያስቀጣ አዋጅ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል። አዋጁም በቀጣይ በጀት ዓመት ጸድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

አዋጁ ቤት የሌላቸው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ፣ በህገ ወጥ መንገድ ቤት የወሰዱና ለመውሰድ የሚሞክሩትን ተጠያቂ የሚያደርግና ጠቋሚዎች የሚጠቀሙበትን ስርዓት የሚፈጥር ነው። ለመጠቆም ምቹ እንዲሆን በድረ ገጽ ዝርዝሩ ይፋ እንደሚደ ረግም ገልጸዋል።

«ቤቶቹ እየተገነቡ ያሉት ህብረተሰቡ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ በሚከፍለው ግብርና በሚቆጥበው ገንዘብ ነው» ያሉት ሚኒስቴሩ፤ ገንዘቡ ለታለመለት አላማ መዋል አለበት።

መንግስት የአገሪቱን ከተሞች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ለህብረተሰቡ ምቹ እንዲሆኑና በፕላን እንዲመሩ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አቶ መኩሪያ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሳካለት መምጣቱንና በቀጣይም ይህን ጥረቱን በተሻለ ለመስራት ማቀዱን ገልፀዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment