Friday, June 05, 2015

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የመጨረሻ 24 የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ይፋ አደረጉ

(ግንቦት 27/2007, (አዲስ አበባ ))--የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ከአገር ውስጥ የተመረጡትን የመጨረሻ 24 ተጫዋቾችን ይፋ አድርጉ። የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ነገ ግንቦት 28 ቀን 2007 አዲስ አበባ ይገባል።

ዋልያዎቹ ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሌሴቶ ጋር ሰኔ 7 ቀን 2007 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። አሰልጣኝ ዮሃንስ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ 24 ተጫዋቾች ይፋ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላከው መግለጫ ያመለክታል።

በዚህም መሰረት ግብ ጠባቂዎች ታሪኬ ጌትነት ከደደቢት፣ ጀማል ጣሰው ከመከላከያ እና አቤል ማሞ ከሙገር ሲሚንቶ ሆነው ተመርጠዋል። ሥዩም ተስፋዬ፣ አስቻለው ታመነና ተካልኝ ደጀኔ ከደደቢት፣ ዘካሪያስ ቱጂና ሰለሃዲን ባርጊቾ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሙጂድ ቃሲምና ግርማ በቀለ ከሀዋሳ ከነማ፣ በረከት ቦጋለ ከአርባ ምንጭ ከነማ እንዲሁም ሞገስ ታደሰ ከሲዳማ ቡና በተከላካይ መስመር የተመረጡ ናቸው።

በአማካዮች ቦታ ምንተስኖት አዳነና በኃይሉ አሰፋ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጋቶች ፓኖምና አስቻለው ግርማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ፍሬው ሰለሞን ከመከላከያ፣ ብሩክ ቀልቦሬ ከወላይታ ዲቻ፣ራምኬል ሎክ ከኤሌክትሪክ እንዲሁም ኤፍሬም አሻሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመርጠዋል።

በአጥቂ ሥፍራ ቢንያም አሰፋ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ባዬ ገዛኸኝ ከወላይታ ዲቻ፣ ዮናታን ከበደ ከአዳማ ከነማ እንዲሁም ኤፍሬም ቀሬ ከሙገር ሲሚንቶ መመረጣቸውን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ከውጭ ሀገር ክለቦች ከተጠሩት ተጫዋቾች መካከል ዋሊድ አታ በጉዳት ምክንያት መሰለፍ እንደማይችል ነው የተገለጸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ነገ አዲስ አበባ ይገባል። የወዳጅነት ጨዋታው የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  

No comments:

Post a Comment