Friday, April 17, 2015

«አሜሪካ መንግሥትን በሃይል ለመናድ ለሚሞክሩ ቡድኖችና ፓርቲዎች ድጋፍ አታደርግም» - የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፖለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ ዊንዲ ሼርማን

(ሚያዚያ 9/2007, (አዲስ አበባ))--ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ሌሎች ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የተቋቋመን መንግስት በሃይል ለመናድ ለሚሞክሩ ቡድኖችና ፓርቲዎች አሜሪካ ድጋፍ እንደማታደርግ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን አስታወቁ። የሚኒስቴሩ ፖለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ ዊንዲ ሼርማን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።



ጠሪዋ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ አሜሪካ የፖለቲካ ትግሉን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የማያደርግ ማንኛውንም አካል ትቃወማለች። "አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ለሌሎች የሽብር ቡድኖች ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ተከትሎ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መንገድ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትን በኃይል ለመናድ ለሚሞክሩ ፓርቲዎችና ቡድኖችን ምንም አይነት ድጋፍ አታደርግም" ብለዋል።

አገራቸው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ በምርጫ አሸናፊ ሆኖ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ንዶ ሥልጣን ለመያዝ የሚሞክር ማንኛውንም አካል እንደምትቃወም ገልጸው፤ ይህንንም ለመከላከል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንደምትሰራም ባለሥልጣኗ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል በጸረ ሽብር እንቅስቃሴ፤ በኢኮኖሚያዊ እድገትና ከባቢያዊና አለም አቀፋዊ ችግሮች ላይ ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ዊንዲ ሼርማን፤አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራቷን ትቀጥላለች ብለዋል።

አገሪቱ በሽብርተኞች ላይ እየወሰደችው ያለው እርምጃ ስኬታማ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይም በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሻባብን በመታገል ረገድ ስኬታማ ስራዎችን እንዳከናወነች ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን በማደግ ላይ መሆኗን በመጪው ወር የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ አሳታፊ፣ ግልጽና ተዓማኒ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ እየተደረገ ያለው ጥረት መልካም መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምዕተ አመቱን የልማት ግቦች ቀድማ በማሳካትና በየዓመቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ መሆኗን የተናገሩት ባለሥልጣኗ፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በሰላምና መረጋጋት፣ በትምህርትና ጤና መስኮች ዙሪያ በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአካባቢው አገሮች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በመስራት ላይ መሆኗንና ስኬታማ ስራዎች ማስመዝገቧን ተናግረዋል። አሜሪካ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለምታከናውናቸው ስራዎች ቁልፍ አጋር መሆኗን የገለጹት ዶክተር ቴድሮስ፣ አገሮቹ በተለይም በግብርና፣ በንግድ፣ በጥናትና ምርምር ዘርፎች የአገሪቱ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የራሷን ሰላምና እድገት ማስቀጠልን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካና በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከጎረቤትና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቀናጅታ እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment