Thursday, December 25, 2014

ልምምድ ላይ የነበረ የኢትዮጵያ ሄሊኮፕተር በዋና አብራሪው አስገዳጅነት ኤርትራ አረፈ

(Dec, 25 2014, (አዲስ አበባ))--የስልጠና ልምምድ እያደረገ የነበረ አንድ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ ሄሊኮፕተር ከሃዲው አብራሪ ቴክኒሺያኑንና ረዳት አብራሪውን በማስገደድ ኤርትራ ማረፉን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ሄሊኮፕተሩ ባለፈው አርብ ከጧቱ 2 ሰዓት ከ35 ጀምሮ በመደበኛ የስልጠና ልምምድ ላይ ነበር፡፡ ተዋጊ ሄሊኮፕተሩ ከግንኙነት ውጪ በመሆኑ በሰራዊቱ፣ በአካባቢው ማህበረሰብ እና በአጋሮች ለተከታታይ ቀናት እና ሰአታት ፍለጋ ሲደረግለት መቆየቱንም አስታውሷል፡፡

ሆኖም ሄሊኮፕተሩ በዋና አብራሪው አማካኝነት ቴክኒሺያኑንና ረዳት አብራሪውን በማስገደድ ኤርትራ ማረፉን የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ «ልማታዊ መንግስትንና ህዝባችን ድህነትን ተረት እያደረጉ ባሉበትና የመከላከያ ሰራዊታችን በሀገር ውስጥና በአለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝና እየተጎናፀፈ ባለበት ወቅት የሀገሪቱ ጠላቶች የደከመች ኢትዮጵያን ለማየት ሀገሪቷን ለማተራመስ ላይ ታች እያሉ ነው»

ሆኖም መንግስትና ህዝብ ከተያያዙት የልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ለአፍታም ቢሆን ሊያደናቅፍ የሚችል ሁኔታ እንደሌለ መግለጫው አመልክቷል፡፡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም የህገ መንግስቱና የህዝቡ አለኝታና መከታ በመሆን «የሻዕቢያን ተላላኪዎችና ቅጥረኞች በከፍተኛ ህዝባዊነትና ጀግንነት ከተቀበሩበት መቃብር ለአፍታም ቢሆን ቀና እንዳይሉ በማድረግ የሀገሪቱን ሰላምና ልማት እናሳካለን» ብሏል፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ


No comments:

Post a Comment