Friday, September 19, 2014

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ይበልጥ ማጠናከር ትፈልጋለች

(Sep 17, 2014, ( አዲስ አበባ))--ሰርጌይ ላቭሮቭ ሩሲያና ኢትዮጵያ በተለይ በኢንቨስትመንት መስክ በጋራ በመሥራት ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር ተወያይተዋል፤

• በባቡር መስመር ግንባታ ለመሳተፍ ፍላጎቷንም አሳይታለች
ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በጋራ መስራት ፍላጎት እንዳላት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አስታወቁ። ከመሐል አገር ወደ ጅቡቲ በሚገነባው የባቡር መስመር ግንባታ ላይ ሩሲያ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይታለች።

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር በሁለቱ አገሮች የጋራ ግንኙነትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከትናንት በስቲያ ተወያይተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በጋራ በመስራት በአገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ፍላጎቱ አላት።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግጭትን ለመፍታትና ሰላም ለማስክበር በዋነኛነትም በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማረጋገጥ የምታከናውናቸውን ሥራዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል። በተለይ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም የምታደርገውን ያላሰለሰ ጥረት የሩሲያ መንግሥት በእጅጉ የሚያደንቀው መሆኑን አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ለቀጣናውና ለአህጉሩ ሰላም የምታከናውናቸውን ተግባራት ሩሲያ እንደምትደግፍ አስታውቀዋል።

እንደ ሰርጌይ ላቭሮቭ ገለጻ፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በኢንቨስትመንቱ ብቻም ሳይሆን በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በባህል መስክ ለመተባበር ፍላጎት አላት። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፎች በተለይም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በጋራ መሥራት ፍላጎት እንዳላት ለሰርጌይ ላቭሮቭ ገልጸውላቸዋል። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው፤ ውይይቱ ፤ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክረው እንደሆነም ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት የቀጥታ የአየር በረራ በአዲስ አበባና በሞስኮ መካከል ለመጀመር መስማማታቸውን ዶክተር ቴድሮስ ጠቅሰው፣ የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ቢሰማሩ በኢትዮጵያ በኩል አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግላቸውም አስታውቀዋል። በተለይ በኃይል፣ በባቡር መስመር ዝርጋታ የሩሲያ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት መሆኑን በውይይቱ ወቅት መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አመልክተዋል።

ሁለቱ አገራት የአየር በረራ ለመጀመር መስማማታቸው ኢትዮጵያ የአበባ ምርቶቿን በሞስኮ ገበያ የምታቀርብበት ሁኔታ እንዲመቻች መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል። በሁለቱ አገራት መካክል ያለው ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ጉዳይ በተለይም በኢንቨስትመንቱ መስክ የተሻለ መስራት እንዳለባ ቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በዋናነትም ሁለቱ አገሮች በጋራ ኮሚሽናቸው አማካይነት ያከናወኑት ተግባር አጥጋቢ እንደነበር መገምገማቸውን ተናግረዋል።

«በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ብዙ አጀንዳ ያላት አገር ናት» ያሉት አምባሳደር ዲና፤ የሰርጌይ ላቭሮቭ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ኢትዮጵያ በሩሲያ አጀንዳ ውስጥ እንዳለች አመላካች መሆኑንና ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት «ከብሪክስ» አባል አገራት ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ትልቅ በር እንደሚከፍት ገልጸዋል። በገፅታ ግንባታ ረገድም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ነው ያስታወቁት። ሩሲያውያኑ ከመሃል አገር ወደ ጅቡቲ በሚገነባው የባቡር መስመር ግንባታ ላይ ለመሠማራት ፍላጎት እንዳላቸው ማስታወቃቸውንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

ሩሲያ ለአፍሪካ ልማት ሰፊውን ደጋፍ ከሚያደርጉት የብሪክስ አባል አገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ የሁለቱ አገራት በሁሉም መስክ ትስስር ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት። በተለይ ሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንቱ መስክ የበለጠ ለመሥራት ስምምነት ለመፈራረም ያላቸውን ፍላጎትም ማስታወቃቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ አገሮች የፑሽኪንን ሐውልት በቅርቡ

 ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል የሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የኢትዮጵያ ጉብኝት ውጤታማ ውይይት የተደረገበትና የአፍሪካና ሩሲያን የቆየ ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እንደሆነ ተገለጸ። የአፍሪካ ህብረት ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ዶክተር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማና የሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭን ከትናንት በስቲያ የአፍሪካ ህብረትና ሩሲያ ፌዴሬሽን የትብብር የተመለከተውን ሰነድ መፈራረማቸውን የተከታተለው ሪፖርተራችን ወንድወሰን ሽመልስ እንደዘገበው፣ የአፍሪካና የሩሲያ ፌዴሬሽን ትብብር በቅኝ ግዛት ትግል ወቅት መጀመሩ ተገልጿል።

ዲላሚኒ ዙማ እንደተናገሩት፣ አፍሪካውያን ለዛሬው ነጻነታቸው መጎናጸፍ ይኸው የትብብር ግንኙነት የራሱን አሻራ አሳርፏል። ምንም እንኳን ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር ያለው ግንኙነት ለአህጉሪቱ አዲስ ባይሆንም የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግን ትብብሩን ማጠናከር ያስፈልጋል። የሚኒስትሩ ጉብኝትም በአፍሪካ ህብረትና ሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ያለውን ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረው ነው።

የትብብር ውይይታቸው ትኩረት ያደረገው ለአህጉሪቱ ዕድገት ወሳኝ በሆነው በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ወጣቱን ማሰልጠን እንደነበር የተናገሩት ዲላሚኒ ዙማ፣ ይህ የትብብር አቅጣጫም አንድና ነጠላ ሳይሆን ለበርካታ ጉዳዮች መሰረትና ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል። ለአብነትም በመሰረተ ልማት፣ ኢነርጂ፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንና ሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች አህጉሪቱ የተማረ የሰው ኃይልና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ እንደሚያስፈልጋትም አመልክተዋል።

የትብብር መስኩም እነዚህን ሊያሟላ የሚችል ቁልፍ መስመር እንደሆነ ያብራሩት ዲላሚኒ ዙማ፣ ይህም በአህጉሪቱ ጠንካራ መሰረተ ልማት እንዲኖር፣ ግብርናውን በማሻሻል የኢኮኖሚ ሽግግሩ እንዲፋጠን፣ ከማዕድንና መሰል የተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያደርጋት እንደሆነም ገልጸዋል። ሩሲያ ቀድሞ የነበራት የትምህርት ትብብር እንዳለ ሆኖ በመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት በሚኖራት ተሳትፎ ላይ መነጋገራቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር ዙማ ገለጻ፣ በትብብር አቅጣጫው በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና የትምህርት ዘርፎች ላይ ከማተኮሩ ባሻገርም አፍሪካና ሩሲያ በአህጉሪቱ የተረጋጋ ሰላም ለማስፈንና ለማረጋገጥ በጋራ የሚሰሩ ይሆናል። ለአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ ለሚኖረው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠልም የሩሲያ ፌዴሬሽን በገንዘብ፣ ቁሳቁስና ስልጠና ጭምር ለመርዳት ዝግጁነቱን ገልጿል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር በኢትዮ ሩሲያ የሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት ከህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር ያደረጉት የአህጉራዊ ትብብር ውይይት አስደሳችና ውጤታማ በመሆኑ እጅጉን መርካታቸውን ተናግረዋል።

እንደ ሰርጌይ ላቭሮቭ ገለጻ፣ የአፍሪካ ኀብረትና ሩሲያ ፌዴሬሽን ትብብር በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ እንደመሆኑ በቀጣይ ይህን ትብብር በተሻለ መልኩ በሚያድግበትና ተጠናክሮ በሚቀጥልበት እንዲሁም ቅድሚያ በሚሰጣቸው የትብብር አቅጣጫዎችና የድጋፍ አሰጣጦች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል። በመሆኑም ሩሲያ የአፍሪካን ኢኮኖሚ በማሳደግ በኩል የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣና ኩባንያዎቿና ባለሀብቶቿ በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ሩሲያና አፍሪካ ቀደም ሲል የነበራቸውን የትምህርት፣ የሰብዓዊ አገልግሎት፣ የባህልና መሰል ዘርፎች የላቀ ትብብር በቀጣይም በተለይ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት አጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል። የኑክሌር ኃይልን ለልማት በሚውልበት አቅጣጫ ላይም ይሰራል። በውሃ ኃይል ማመንጫና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይም ይሳተፋል። በመሆኑም ሩሲያ በአፍሪካ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖር የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች።

በአፍሪካና ሩሲያ መካከል ለሚኖረው ፖለቲካዊ የጋራ ተጠቃሚነት የተሻለ ነገርን ለመፍጠርና በዓለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መስመር ለመያዝ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment