Tuesday, July 08, 2014

የግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት አመራር በቁጥጥር ስር ዋለ

(ሐምሌ 1/2006, አዲስ አበባ ))--በሽብር ወንጀል ተከሶ በተደጋጋሚ የተፈረደበትና በኢትዮጵያ መንግሥት በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው የግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት አመራር አንዳርጋቸው ጽጌ በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን የብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ጸረ ሽብር ግብር ኃይል አስታወቀ።



በየመን እና በኢትዮጵያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት መካከል በጸረ ሽብር ትግል ተቀናጅተው ለመስራት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሁለቱ ተቋማት አሸባሪዎችን በመያዝና በመለዋወጥ ይሰራሉ።

በዚህም መሰረት የተፈላጊ ወንጀለኛው የጉዞ መስመርና የሚጓዝበትን ዕለት አስቀድሞ መረጃ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት መረጃውን ለአጋር የየመን ብሄራዊ የደህንነት ቢሮ በማሳወቅ በሰንዓ በኩል ወደ ኤርትራ ሊገባ ሲል ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውሎ በዚያው ዕለት ለኢትዮጵያ ተላልፎ ተሰጥቷል።

ቱፋ፣ ጅን ፓወል፣ ደርባባ፣ ጀምስ ፍራንኪ፣ ሮቢ እና ወዲ-ሓሬና በሚባሉ የተለያዩ የሽብር የምስጢር ስሞች ሲጠቀም የቆየው ይኸው የአሸባሪ ድርጅቱ አመራር ከአምስት ዓመት በላይ በቋሚነት ኤርትራ ውስጥ መሽጎ ከሻዕቢያና ከሌላ ጸረ ኢትዮጵያ ከሆነ መንግሥት ጋር በመቀናጀት፣ አሸባሪዎችን በማደራጀትና በማሰልጠን የአገሪቷን ሠላም ለማደፍረስና ልማቷን ለማደናቀፍ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል።

ከዚህ በፊት እንደሚታወሰው በአንዳርጋቸው ጽጌና በኤርትራ መንግሥት ለወራት ያህል የፈንጂ ስልጠና ወስዶ ወደ አገር ውስጥ የገባው አበበ ወንድማገኝ የተባለ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በድንበር በኩል ከኤርትራ የተላከለትን ፈንጂ በመጠቀም ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ የሽብር ጥቃት በመፈጸም በበርካታ ሠላማዊ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ዝግጅት ሲያደርግ ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም ከነግብረ አበሮቹ እና የፈንጂ ቁሳቁሱ እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦና ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ የእስር ቅጣት እንደተበየነበት ይታወቃል።

አሸባሪው አበበ ወንድማገኝን ከእንግሊዝ በመመልመል ለፈንጂ ስልጠና ወደ ኤርትራ የላከው በአንዳርጋቸው ጽጌ ስር የኦፕሬሽን ኃላፊ ተብሎ የተመደበው ሻለቃ ማሞ ለማ የተባለ ሌላ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንደነበር የሚታወቅ ነው።

በአገር ውስጥም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግሥት ባጎናጸፋቸው የመደራጀት መብት መሰረት ህጋዊ መብታቸው ተረጋግጦላቸው በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው በአሸባሪነት ከተፈረጀው ከግንቦት 7 እና የድርጅቱ ልሳን ከሆነው የኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ግንኙነት በማድረግ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎችም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዛሬ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በዚህ አጋጣሚ የሌላ አገር ዜግነትን፣ የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነትን፣ጋዜጠኝነትን እና የመሳሰሉትን በሽፋንነት በመጠቀም በሽብር ተግባር ላይ መሳተፍ፣ ከህግ ተጠያቂነት ሊያስጥል እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል ሲል የብሔራዊ መረጃና የደህንነት አገልግሎት እና የፌዴራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

Related topics:
የእንግሊዝ መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መተላለፋቸውን መስማቱን አስታወቀ 
  

No comments:

Post a Comment