Friday, June 14, 2013

ዋሊያዎቹ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

(June 14, 2013, (አዲስ አበባ))--ከዋሊያዎቹ አንዳንድ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ለእሁድ ጨዋታ መድረስ ባይችሉም ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ልምምዳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፤ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድናቸው በእሁድ ጨዋታ ውጤቱን ጠብቆ ለመውጣት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፤

ብራዚል በአውሮፓውያኑ 2014 ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ዋሊያዎቹ ከነገ በስቲያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድናቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ እንደሚያደርግ ሲገልጹ ቡድኑን በአምበልነት እንደሚመራ የሚጠበቀው አይናለም ኃይሉ ቡድኑ ጨዋታውን በድል እንደሚወጣ ገልጿል።

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እየተሳተፉ ከሚገኙት የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ከነገ በስቲያ አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቧል ።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ባለፈው ቅዳሜ ከሜዳቸው ውጪ ያደረጉትን ጨዋታ አሸንፈው የሚገኙ መሆናቸውና የደረጃ ሠንጠረዡን አንደኛና ሁለተኛ ሆነው መምራታቸው ጨዋታው የሚጠበቅ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይገኙበታል ።

በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእሁዱን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ለመጨረሻውና ለጥሎ ማለፉ መድረሱን የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ የምትሸነፍ ከሆን በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ የመሳተፍ ህልሟ ሙሉ ለሙሉ የሚያከትም መሆኑም ሌላው ጨዋታው በጉጉት እንዲጠበቅ ምክንያት ከሆኑት መካከል ይገኝበታል።

የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድኑ ለጨዋታው በማድረግ ላይ የሚገኘውን ዝግጅት አስመልክቶ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በእሁዱ ጨዋታ ቡድናቸው  ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በመጫወት ውጤት ይዞ ለመውጣት ጥረት ያደርጋል ።

«ውድድር ሲደረግ ቀላል የሚባል ቡድን የለም » ያሉት አሰልጣኝ ሰውነት፣ ጨዋታው ከባድ እንደሆነም ተናግረዋል።  ደቡብ አፍ ሪካ በእግር ኳስ ከኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ  እንደምትገኝና  ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ተፎካካሪነትና ውጤታማነት እየመጣች መሆኗን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አመልክተዋል። የእሁዱ ጨዋታ ከባድ መሆኑን አብራርተው፣ ቡድናቸው ከቦትስዋና መልስ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት ።

ቡድናቸው ለረጅም ጊዜ አብሮ የቆየ በመሆኑ ተጫዋቾች ቢጎዱ እንኳ ሊተኳቸው የሚችሉ ተመጣጣኝ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች እንደሚገኙም ጠቁመዋል። ተጫዋቾቻቸው ለጨዋታው ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነቱም እንዳላቸው የተናገሩት አሰልጣኝ ሰውነት፣ በእሁዱ ጨዋታ በጨዋታው ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ገልጸዋል።

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማካተቱንና አዲስ ተጫዋች ደግሞ ለመታወቅ ያለውን ሁሉ እንደሚሰጥ አሰልጣኙ ጠቅሰው፣ « ማንም ይሁን ማን በእጃችን የገባውን እድል አሳልፈን ላለመስጠት የምንችለውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን » ብለዋል።

ተጫዋቾቻቸው በጥሩ የሥነ ልቡና ዝግጅት ላይ እንደሚገኙና አምበሉ ደጉ ደበበ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አለማገገሙንና አበባው ቡጣቆም የተወሰነ ጉዳት እንዳለበት ተናግረዋል።ይሁንና እንደ የቦታው በቂና ተመጣጣኝ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለም አሰልጣኙ ያመለክታሉ።

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በሜዳው አንድም ግብ ያልተቆጠረበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሁንም በእሁዱ ጨዋታ በሜዳው ግብ እንዳይቆጠርበት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት ። ደጋፊው ሙሉ የጨዋታ ጊዜውን ሁሉ ለቡድኑ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረቡት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ፣ቦትስዋና ላይ ባደረጉት ጨዋታ የተጋጣሚያቸው ደጋፊዎች ቡድናቸው ሁለት ለባዶ ሲመራና ተሸንፎ ሲወጣ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳልተለየው ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።

የተጋጣሚያቸው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጎርደን ኢግሰንድን ጨምሮ የቡድኑ የአማካይ ክፍል ተጫዋች የሆነው ሲፊዌ ሻባላላን የመሳሰሉ ተጫዋቾች በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ማሸነፍ ከባድ ነው በማለት የሚሰጡት አስተያየት የማዘናጊያ ነው ብለዋል። ይህንን አባባል የሚያምኑት በጨዋታው ሲያሸንፉ ብቻ እንደሆነም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስረድተዋል።

በቦትስዋናው ጨዋታ የዋሊያዎቹ አምበል ደጉ ደበበ በድንገት የደረሰበትን ጉዳት ተከትሎ ቡድኑን በአምበልነት የመራው የደደቢቱ አይናለም ኃይሉ በበኩሉ ጨዋታውን በድል እንደሚያጠናቅቁ ያለውን እምነት ገልጿል። የቡድኑ አባላት የእሁዱን ጨዋታ በድል ለማጠናቀቅ ጠንክረው በመስራት ላይ እንደሚገኙ አይናለም ገልጾ፣ የቡድኑ አባላት በሙሉ ይህንን ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸውም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ከሜዳው ውጪ አቻ መውጣቱን ያስታወሰው አይናለም ፣ቡድኑ ባፋና ባፋናዎችን ባላቸው ስም ብቻ አክብዶ እንደማያያቸው ገልጿል። የቡድኑ ተጫዋቾች በአገራቸውና በሕዝባቸው ፊት የሚያደርጉትን ጨዋታ ለማሸነፍ እንደሚጥሩና ይህም እንደሚሳካላቸው ቡድኑን በአምበልነት ሊመራ እንደሚችል የሚጠበቀው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አይናለም አብራርቷል።

ቦትስዋና ፣መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙበትን ምድብ አንድን ዋሊያዎቹ ከአራት ጨዋታዎች በሰበሰቧቸው አስር ነጥቦች  በመምራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ፣የእሁዱ ተጋጣሚያቸው የደቡብ አፍሪካው ባፋና ባፋና በስምንት ነጥብ በመከተል ላይ ይገኛል።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment