Tuesday, May 14, 2013

የፀረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል

(May 14, 2013, (አዲስ አበባ))--የኢፌዴሪ መንግሥት ሙስናን በመከላከል የአገሪቷን እድገት ይበልጥ ለማፋጠን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት፤ መንግሥት ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ፈጣን ልማት ለማስቀጠል፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሙስናን በቁርጠኝነት ለመዋጋት እየሰራ ነው።

መንግሥት ሙስናን ለመከላከል ሲያከናውን የቆየውን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል መወሰኑን የተናገሩት ከፍተኛው የሥራ ኃላፊው፤ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ባለፈው መጋቢት ባካሄደው ዘጠነኛው ጉባዔ ላይ የኪራይ ሰብሳቢነትና ተግባር በቁርጠኝነት ለመዋጋት መወሰኑንም አስታውሰዋል።

በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉንና ይህም መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት እያደረገው ያለው ጥረት አንዱ አካል መሆኑን አመልክተው፤ ሥልጣንን አለአግባብ ተጠቅሞ  የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር  የሚፈጽም ማንኛውም የሥራ  ኃላፊ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ አመልክተዋል።

«ከዚህ በፊትም ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው የሙስና ወንጀል በፈጽሙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ መንግሥት እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል» ያሉት ባለሥልጣኑ፣ በቅርቡ የተወሰደውን እርምጃ በገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩትን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች በመከላከል የአገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment