Tuesday, February 05, 2013

በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻልና ተከባብሮ የመኖር እሴት ተጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ቤተ እምነቶች ጠንካራ ርብርብ ማድረግ አለባቸው

(አዲስ አበባ ጥር 27/2005)--ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበረው የሃይማኖት መቻቻልና ተከባብሮ የመኖር እሴት ተጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ቤተ እምነቶች ጠንካራ ርብርብ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር አሳሰቡ። 


ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በሐይማኖት መቻቻል ዙሪያ ከተለያዩ የሐይማኖት መሪዎችና ማህበራት ጋር አዲስ አበባ ውስጥ በተደረገው ውይይት ላይ እንደገለጹት ሁሉም ቤተ እምነቶች ምእመናን አስተባብረው በአገሪቱ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ በተጀመረው ርብርብ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ ማስተማራቸውን መቀጠል ይገባቸዋል።


 በአገሪቷ ለዘመናት የቆየውን የመቻቻል እሴት በተቋም ደረጃ በማሳደግ የሁሉም ኃይማኖት ተከታዮች በመቻቻል መርህ ላይ ተመሰርተው ቀጣይ ጥረቶች እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። ኃይማኖቶች ሰላምን በመስበክ፣ ልማትን በማፋጠንና አንድነትን በማጠናከር በአገሪቱ የተሻለ ማህበራዊ መግባባት እንዲፈጠር የጀመሩትን ገንቢ ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል። 

መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ በህገ-መንግስቱ ጭምር በተረጋገጠው መርህ ላይ ጥርጣሬና ብዥታ እንዲፈጠር የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉ ያብራሩት ሚኒስትሩ ይህን የሚያናፍሱ አካላት የራሳቸውን ድብቅ አላማ ለማስፈጸም በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ሃይሎች እንደሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ሊገነዘብ ይገባዋል ብለዋል። ዶክተር ሽፈራው እንዳብራሩት የሃይማኖት አክራሪነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንጂ ሃይማኖታዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማቱ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥና የማስተማር ስራዎቻቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል። 

ኢዜአ ያነጋገራቸውና በውይይቱ የተሳተፉ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች እንዳሉት ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት በመቻቻል፣መከባባርና በመደጋገፍ አብረው የኖሩ ህዝቦች በመሆናቸው በአገሪቱ በእምነት ሳቢያ የእርስ በርስ ግጭት ተከስቶ አይታወቅም። በአገሪቱ በኃይማኖቶች ሽፋን አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችና ግጭቶችም በውጭ ባዕዳን ኃይሎች እንጂ በኢትዮጵያውያን አነሳሽነት የሚከሰቱ አለመሆናቸውን የኃይማኖት አባቶቹ ገልጸዋል። 

የአገሪቱ ሰላም እንዲደፈርስና የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዳይቀጥሉ አንዳንድ ጸረ¬¬-ሰላም ወገኖች በውጭ ተቋማት ጭምር እየተጋዙ በህብረተሰቡና በአገሪቱ ላይ እየፈጸሙት ያለው ተግባር በሁሉም ቤተ-እምነቶች ተቀባይነት የሌለውና አደገኛ መሆኑን አባቶች ገልጸዋል። የተጀመረውን ፈጣን ልማት ወደ ኋላ እንዳይጓተት ሁሉም ቤተ እምነቶች በጋራ ተቀራርበው ለመስራትና ችግሮች ሲያጋጥሙ በምክክር የሚስተካከሉበት ዘዴ በቋሚነት መመሰረት እንደሚገባም አመልክተዋል። 

በኃይማኖት ሽፋን የሚፈጸሙ የአክራሪነት ድርጊቶችን በጋራ በመታገል በኅብረተሰቡ መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አንድነትና የመደጋጋፍ ባህል የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውንም አባቶቹ ገልጸዋል። ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በየሶሰት ወሩ በሰላም ግንባታ ላይ በጋራ ተቀራርበው የሚሰሩበት መድረክ እንዲኖርም ተስማምተዋል። 
ኢዜአ 

No comments:

Post a Comment