Sunday, February 03, 2013

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

(አዲስ አበባ ጥር 24/2005)--በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጥሩ ተሳትፎ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲዬም ደማቅ አቀባበል ተደረገለት። ለቡድኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች አካላት ከደቡብ አፍሪካ ሲመለስ የአበባ ጉንጉን በመስጠት ደማቅ አድርገውለታል። 



ለኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ደማቅ አቀባበል ተደረገለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በዚሁ ጊዜ ቡድኑ ምንም እንኳን ወደ ቀጣይ ዙር ባያልፍም ከ31 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን በእግር ኳስ መድረክ በማራኪ ጨዋታ ለዓለም በማሳየት ከፍተኛ ኩራት ለሕዝቡ ማጎናጸፉን ተናግረዋል።

በቀጣይ በሚኖሩት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች አልፎ ወደ ብራዚል ለመጓዝም ቡድኑ ጠንክሮ በመሥራት የአገሪቱን እግር ኳስ ደረጃ በይበልጥ ከፍ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የስፖርት ኮሚሽነር አቶ አብዲሳ ያደታ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ቡድኑን በሞራል በማበረታታት ቡድኑ ለወደፊት ጠንክሮ እንዲሰራና ተተኪ ተጫዋቾችን በብዛት ለማፍራት እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለብሔራዊ ቡድኑ የሰጡት ድጋፍ ለአገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር መግለጻቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ''የደቡበ አፍሪካ ቆይታችን ጥሩ ነበር ብዬ አምናለሁ። ለወደፊት ለምናደርጋቸው ውድድሮችም ትልቅ ልምድ አግኝተንበታል'' ብለዋል፡፡ ''በአንደኝነት የምንመራውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ከምድቡ ጠንክረን በመሥራት በብራዚል የዓለም ዋንጫ ላይ መሳተፍ እንፈልጋለን'' ሲሉም ተናግረዋል። 

ለብሔራዊ ቡድኑ ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው አዳነ ግርማ በሰጠው አሰተያየት'' እግሬን ተጎድቼ ለብሔራዊ ቡድኑ የምፈልገውን አስተዋጽኦ ባለማድረጌ አዝኛለሁ። ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረጉት ውድድሮች ላይ ጥሩ ብቃት በማሳየት ሕዝቤን ማስደሰት እፈልጋለሁ'' ብሏል።

''በደቡበ አፍሪካ የነበረው አትዮጵያዊ ተመልካች ብዛት ኢትዮጵያ ወስጥ የምንጫወት ሆኖ እንዲሰማን አድርጓል'' ሲልም አክሎበታል። የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ በበኩሉ በሕዝብና በመንግሥት የተደረገላቸው አቀባበል ብሔራዊ ቡድኑ አደራን እንዲሸከም እንዳደረጋቸው መናገሩን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

በብሄራዊ ቡድኑ አቀባበል ሥነ ሥርዓት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ተገኝተዋል።  
ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  

No comments:

Post a Comment