Wednesday, January 30, 2013

የዋልያዎቹ ክራሞት

(Jan 30, 2013 ተጻፈ በ  ደረጄ ጠገናው)--የአገሬው ሰው ከ2010 የዓለም ዋንጫ ትውስታ የተላቀቀ አይመስልም፡፡ 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ያስተናገደው ግዙፍ ሶከር ሲቲ ስታዲየም አልፎ አልፎ ካልሆነ ብዙዎቹ ወንበሮች ሰው አልባ ነበሩ፡፡


በስታዲየሙ ካሉት ታዳሚዎች ከአገሬው ሰው ይልቅ በየአቅጣጫው የሚታዩትን የስታዲየሙን ድባብ በማድመቅ ቀልብ የሚስቡት በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የተዋቡት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ የዋልያዎቹ መለያ ይቸበቸባል፡፡ ይዘፈናል፣ ደስታ ይንፀባረቃል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑት የኢትዮጵያ ልጆች ስሜት ለባዕዳውያን ብቻ ሳይሆን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አብረን ለተጓዝነው አስደማሚና አስገራሚ ነበር፡፡

አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በሐበሾቹ መንደር ብቻ ሳይሆን በተንቀሳቀስኩባቸው ሁሉ ተመልክቻለሁ፡፡ ቩቩዜላ ይነፋል፡፡ ውቦቹ የሐበሻ ሴቶች፣ ሀብታም ኢትዮጵያውያንና ወጣቶች ባቋቋሙት አስተባባሪ ኮሚቴ እየተመሩ ከ31 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዋንጫ ላበቁትን ዋልያዎች የሞራል ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅት ከጀመሩ መሰነባበታቸውን ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ምናልባትም ኢትዮጵያ በ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ባትሳተፍ ኖሮ፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) “ኦሬንጅ አፍሪካ ካፕ ኦፍ ኔሽን” ሲል የሰየመው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዘመናዊዎቹ የደቡብ አፍሪካ ስታዲየሞች ከመታየቱ ባለፈ የተመልካች ድባቡ ምን ሊመስል ይችል እንደነበር ራሴን ሳይቀር እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡

ለዘመናት በቅኝ ግዛት ተይዛ የቆየችው ደቡብ አፍሪካ በመሠረተ ልማት እንከን አይወጣላትም፡፡ የአገሬ ሰው “ለምለሚቷ አገሬ” እያለ የሚያንጎራጉረው ይገልጻታል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ለ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ግምት የሰጡ ባይመስሉም፤ በበረራ ቁጥር ET 809 የተመዘገበው የኢትዮጵያ ቦይንግ 777 ጀት አውሮፕላን ዓርብ ጥር 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በ5 ሰዓት ከ20 ተነስቶ ከአምስት ሰዓት በረራ በኋላ ጆሐንስበርግ ሲደርስ አካባቢው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በያዙ ሰዎች ተጥለቅልቆ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ገብተን ምን ማድረግ እንደነበረብን ያወቅነው ከሰዓታት በኋላ ነበር፡፡

የማይጨበጡት ዋልያዎቹ
እስከ ደቡብ አፍሪካው ኦሊቨር ታምቦ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ድረስ አብረውን የዘለቁት ዋልያዎቹና ልዑካን ቡድኑ በዕለቱ ከጆሐንስበርግ 370 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ኔልሰፕሪዮት ከተማ መብረር ነበረባቸው፡፡

ከዋልያዎቹ ጋር ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተጓዝነው ጋዜጠኞች ውስጥ ከሦስቱ በስተቀር ሁላችንም ማረፊያችንን ያደረግነው በጆሐንስበርግ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኛው ጋዜጠኛ ስለዋልያዎቹ ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ የሚደርሰው ከጋዜጦችና ከሱፐር ስፖርት ካልሆነ በስማ በለው ነው፡፡ ዋልያዎቹ ከፕሬስ አታሼ ጀምሮ የተሟላ ልዑካን እንዳላቸው ቢታወቅም ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ክፍተት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ከዛምቢያ አቻው ጋር በምቦምቤላ ስታዲየም ለነበረበት የመጀመሪያው ጨዋታ፤ ጋዜጠኞች ለመዘገብ ከጆሐንስበርግ 370 ኪሎ ሜትር ወደሚርቀው ኔልስፕሩት ደርሶ መልስ 12 ሺሕ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ለመክፈል ተገደናል፡፡

ከጆሐንስበርግ እስከ ኔልስፕሩት ደረቱን የሰጠው አውራ ጎዳና ከአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቅ ዓላማ ውጪ አይስተዋልበትም፡፡ ውቦቹ ኢትዮጵያውያት ሳይቀሩ ደስታቸውን የሚገልጹበት ድባብም የተለየ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ ብዙ ከተወራለት ዛምቢያ ጋር አንድ ተጫዋች በቀይ ወጥቶባቸው ነጥብ ተጋርተው ወጡ፡፡ ሱፐር ስፖርት ውድድሩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የመረጣቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ኮከብ ሰንዴይ ኦሊሼና ሌሎችም ለዋልያዎቹ እንቅስቃሴ አድናቆታቸውን ሰጡ፡፡ 

የዛምቢያው ጨዋታ ዋልያዎቹ ከቡርኪና ፋሶ ጋር በቀጣይ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት እንዲጠበቅ አደረገው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዋልያዎቹ የነበራቸውን ክብርና አድናቆት የቡርኪና ፋሶ ጨዋታ እስከተደረገበት ዓርብ ጥር 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ የሚገልጹት እንቅስቅሴና የአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ገድል በመተረክ ነበር፡፡

የማይጨበጡት ዋልያዎቹ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ወኔ ብቻ ሳይሆን ከኳስ ጋር የነበራቸው ቁርኝት ሳይቀር ለጥርጣሬ በቃ፡፡ ዕድሜ ለኤርትራዊው የመስመር ዳኛ የቡርኪና ፋሶ ተጫዋቾች ቁጥር በአንድ ቢቀንስም ዋልያዎቹ ክፍተቱን ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ አሠልጣኝ ሰውነት ከጨዋታው በኋላ “በቃ ከእንግዲህ ማሰብ ያለብን ስለቀጣዩ ጨዋታ ነው” ከማለት ያለፈ አንዳችም አላሉም፡፡ በማግስቱ ከዋልያዎቹ ጋር አብሮ የተጓዘው የቴክኒክ አማካሪዎች፣ ሁለቱ አሠልጣኞችና የቡድን መሪው በጨዋታው ዙሪያ ስብሰባ አድርገው አሠልጣኝ ሰውነት “ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ እንዲያደርጉ የተነገራቸውን ትተው በራሳቸው መንቀሳቀሳቸው” ለውጤቱ ምክንያት ስለመሆኑ እንዳስረዱ ለማወቅ ችያለሁ፡፡

ከተጫዋቾቹ አንዳንዶቹ ደግሞ በተለይም የቡድኑ ድክመት ጎልቶ የታየበት ተከላካይ ክፍል ኳስ ተረጋግቶ ሊያቀብል የሚችል አማካይ ባለመኖሩ ጫናው ሊበረታ መቻሉን ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መድረኩን የተቀላቀለው ከ31 ዓመት በኋላ ነው፡፡ ጎል ማግባት የቻለው ደግሞ ከ37 ዓመት በኋላ ነው፡፡ የአገሪቱ እግር ኳስ ከተሠራበት ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ምልክቶች አሉ፡፡ በመሆኑም መሆን ያለበት የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት ከድክመቱ መማር እንጂ አሠልጣኝ፣ ተጫዋች፣ ፌዴሬሽን እየተባሉ መቀጠሉ ዋጋ እንደሌለው ነው፡፡
በደረጀ ጠገናው ከደቡብ አፍሪካ

No comments:

Post a Comment